Mols.gov.et

mols mols

News

የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ ፀደቀ

የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ ፀደቀ
የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) 114ኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በጄኔቫ ሲጠናቀቅ፣ በዲጂታል ዘመን የሥራ ገበያን የሚመራ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ (Convention) በሰፊ ድምፅ በማፅደቅ ታሪካዊ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ይህ አዲስ ኮንቬንሽን በዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ የሚመሠረት ሥራ (platform work) ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች የሥራ መብት፣ የሥራ ደህንነት፣ የፍትሃዊ ክፍያ እና የማህበራዊ ጥበቃ መርሆዎችን ለማጠናከር ዓለም አቀፍ መሠረት ይጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ንቁ ተሳትፎ አድርጓል፡፡
ልዑካኑ በአሠሪዎችና በሠራተኞች ኮንፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ በመሆን በተለያዩ ኮሚቴዎች ውይይቶች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
በውይይቶቹ የተነሱት ዋና ጉዳዮች መካከል የዲጂታል እና ፕላትፎርም ኢኮኖሚ ሽግግር፣ የሴቶች እኩል ተሳትፎ እና ጥቅም ማረጋገጥ፣ እንዲሁም ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን በማጠናከር ምርታማነትን ማሳደግ ይገኙበታል፡፡
አዲሱ የተፀደቀው ዓለም አቀፍ የሥራ ደረጃ በተለይ በፈጣን የዲጂታል ዘመን ላይ የሚሰሩ ሠራተኞች በግልፅ የሥራ መብት እና የጥበቃ ስርዓት እንዲያገኙ የሚያስችል የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል በዲጂታል እና በአረንጓዴ የልማት ሽግግሮች ወቅት ሴቶች እኩል የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥርዓታዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በመንግስታት፣ በአሠሪዎች እና በሠራተኞች መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስታንዳርዶችን ማሻሻል ሌላው የተወያዩበት ዋና ነጥብ ነበር፡፡

Read More »
News

የሚሻሻለው የውጭ ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ…

የሚሻሻለው የውጭ ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ መመሪያ በሂደት የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን መተካት የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ አሰጣጥን ለማሻሻል ባዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል። ይህ አዲስ መመሪያ በሂደት የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን መተካት የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
በመድረኩ የተገኙት በሚኒስቴሩ የሥራ ስምሪት ማስፋፍያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ፈረዳ እንደገለጹት፤ መመሪያው የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የግል ዘርፉን የሚያበረታታ እና የሀገር ውስጥ ሠራተኞችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ተዘጋጅቷል።
አክለውም እስካሁን በሥራ ላይ የነበረው መመሪያ የቆየ በመሆኑ አሁን ላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከሚጠይቀው ፍላጎት አንጻር መመሪያውን ማሻሻልና ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ በበኩላቸው፣ መመሪያው አዲሱን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ሊሸፈኑ በማይችሉ ልዩ የሙያ መስኮች ላይ ብቻ የውጭ ዜጎችን በመቅጠር የሥራ ገበያውን ክፍተት ከመሙላት ባሻገር የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን በሂደት መተካት የሚችሉ ብቁ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት አላማው አድርጓል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የውጭ ዜጎች ያለአግባብ ወደ ሥራ ገበያው እንዳይገቡና የዜጎችን የሥራ ዕድል እንዳያጠቡ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እና ከታኅሣሥ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውን መመሪያ ከአዲሱ የአዋጅ ሥልጣን (አዋጅ ቁጥር 1156/2011) ጋር እንዲጣጣም እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

Read More »
News

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያዘጋጀው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ…

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያዘጋጀው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ‹‹አካታችነት››ን ዋንኛ ምሰሶ ለማድረግ የሚያግዝ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ አካሄደ
በመድረኩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የስትራቴጂክ ዕቅድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢብርሂም ሰይፉ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚያስፈፅማቸው የክህሎት ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ዘርፎች ሴቶችን፣ ወጣቶችን አካል ጉዳተኞችንና ሌሎችን ተጋላጭ የህበረተሰብ ክፍሎች ላይ በይበልጥ የሚያተኩሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚቀረፁ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና መመሪያዎች ከዚሁ አንፃር የተቃኙ ከመሆናቸውም በላይ አዲሱ የዘርፉ እሳቤ ውስጥም አካታችነት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ዜጎችን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሚኒስቴር መ/ቤቱ እያዘጋጀ በሚገኘው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ውስጥ አካታችነት ዋንኛ ምሰሶ እንዲሆን ለማስቻል መድረኩ በሴቶችና አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚዘጋጁ ዕቅዶችና አፈፃፀሞች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሚገባ እንዲያካትቱ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ከአካቶ ትግበራ አንፃር ሰፊ የአመለካለካከትና የተግባር ክፍተት የሚስተዋል በመሆኑ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት መሰራት እንደሚኖርባቸውም በተወያዮች ተመላክቷል፡፡
አካታችነት ላይ ያተኮሩ ትክክለኛ መረጃዎችን ማሰባሰብና በተለያየ አጋጣሚ የሚገኙ መረጃዎችንም ዜጎችን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም በአፅንኦት ተነስቷል፡፡

Read More »
News

በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ ላይ …

በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጀርመን የልማት ድርጅት(GIZ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ‹‹በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ›› ዙሪያ የሚያተኩር አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ከግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችና ጉዳዩ የሚመለከታው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳታፊ የሆኑበትን ይህን መድረክ በንግግር የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዜጎችን የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሪፎርም ሥራዎችን በቁርጠኝነት እያከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ዜጎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ተገቢውንና ክብር ያለው የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከነዚህ ስትራቴጂካዊ ሪፎርሞች መካከል ግንባር ቀደሙ የሥራ ገበያውን ዘመናዊና ተደራሽ ማድረግ ሲሆን፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (E-LMIS) የመበልጸግ ሥራ ተጠናቆ፣ ሥራና ሠራተኛ በዲጂታል ፕላትፎርም በቀላሉ የሚገናኙበት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል፡፡
መንግሥት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ለመወሰን መመሪያ ቁጥር 45/2013 አዘጋጅቶ ባለፉት አምስት ዓመታት ሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም አተገባበር ላይ በተደረጉ ዳሰሳ ጥናቶች የአፈጻጸም ክፍተቶችና ውስንነቶች መስተዋላቸውን ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችና የመብት ጥሰቶች መኖራቸውን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ጠቁመዋል፡፡
‹‹የመብት ጥሰት በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ ሲቀርብ፣ መንግሥት አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ያለማወላወል እንደሚወሰድ ሁሉም ወገን ሊገነዘበው ይገባል” ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የተሸሻለው መመሪያ ሠራተኛውን፣ አሠሪውንና ኤጀንሲዎችን በእኩልነትና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለተግባራዊነቱ ርብርብ እንዲያደርጉ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

Read More »
News

በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ከፍተኛ ውጤ

በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ
በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ የጥናትና ምርምር ጉባኤ እና የቴክኖሎጂ ውድድር፣ ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።
ከሰኔ 5 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ መድረክ ከ10 አገራት የቀረቡ 35 የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ 6ቱ ለፍጻሜ የደረሱ ሲሆን፣ 4ቱ ከኢትዮጵያ፣ 1 ከሕንድ እና 1 ከናይጄሪያ ነበሩ።
በመጨረሻው ውድድር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርናን ለማጎልበት የሚያስችል በIoT ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የመስኖ ክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ያቀረበው ዘላለም እንዳለው አንደኛ ደረጃን በመያዝ የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
አካልን ሳይጎዳ የጭንቅላት ውስጥ ግፊትን ለመለካት የሚያስችል CEREBRO-LOGIC የተሰኘ ፈጠራ ያቀረቡት ሩት ጌታቸው፣ ሀመረ፣ ያብስራ እና ሪሀና ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከናይጄሪያ የቀረበው የገቢ መረጃና ተከታታይነት ማረጋገጫ ሥርዓት (Revenue Intelligence and Traceability System) ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን በማግኘት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ለአሸናፊዎቹ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት፣ ውጤቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች በምርምር፣ በክህሎትና በፈጠራ ያላቸውን አቅም በግልጽ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የፈጠራ ሥራዎቹ ከውድድር ባሻገር ወደ ሥራ እና ወደ ገበያ እንዲገቡ አስፈላጊ ድጋፎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በማጠቃለያው ሥነ ሥርዓት ላይ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን፣ ለአሸናፊዎችም እንደየደረጃቸው ሜዳሊያና ልዩ ሽልማቶች ተሰጥተዋል።

Read More »
News

ምርምር፣ ፈጠራና አጋርነት የዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረቶች ናቸው ዶ/ር ብሩክ ከድር

ምርምር፣ ፈጠራና አጋርነት የዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረቶች ናቸው
ዶ/ር ብሩክ ከድር
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ምርምር ኮንፈረንስና የቴክኖሎጂ ውድድር በስኬት ተጠናቋል።
መድረኩ ከ16 በላይ ሃገራት ተወዳዳሪዎች፣ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና የዘርፉ ተዋናዮችን በአንድ ያገናኘ ነው።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ብሩክ ከድር በመዝጊያ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምርምር፣ ፈጠራና አጋርነት የዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረቶች ናቸው ብለዋል፡፡
የመጪውን ዘመን ፍላጎት የሚመለስ የክህሎት ልማት ስርዓት ለመገንባት የምርምር ባህልን ማጠናከር፣ ፈጠራን ማበረታታት እና ከኢንዱስትሪ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር ማስፋት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በኮንፈረንሱ 85 የምርምር ጽሑፎች ቀርበው 31 ጥራት ያላቸው ጥናቶች ለመድረክ የተመረጡ ሲሆን፣ 29 የምርምር ሥራዎች በዲጂታል ሽግግር፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ በኢንዱስትሪ 4.0፣ በአረንጓዴ ክህሎቶች፣ በታዳሽ ኃይል እና በአካታች የቴክኒክና ሙያ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በቴክኖሎጂ ውድድሩ ከ10 አገራት የተውጣጡ 35 ፈጠራዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃዎችን በመያዝ እንደ ሃገር ያለንን የፈጠራ አቅም አሳይተዋል።
በቴክኖሎጂ ውድድሩ የIoT Smart Irrigation System አንደኛ ደረጃን ሲያገኝ፣ የCerebro Logic ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። የናይጄሪያው Eco-Bin Revenue Intelligence and Traceability System ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን በማግኘት የነሃስ ሜዳሊያ ተሸልሟል።
በመድረኩ በአንጎል ውስጥ ግፊትን ያለ ቀዶ ሕክምና ለመለካት የሚችለውን Cerebro Logic የተሰኘ ቴክኖሎጂን የሰሩት ወጣት ሴት የፈጠራ ባለሙያዎች ልዩ አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡
የቀረቡት ጥናቶችና ፈጠራዎች በወረቀት ላይ ብቻ ሳይቀሩ ወደ ተግባርና ወደ ገበያ እንዲሸጋገሩ የፈጠራ ማበልጸጊያ ማዕከላት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥርዓቶች እና የምርምር ትብብሮች የበለጠ መጠናከር እንዳለባቸው ዶ/ር ብሩክ አሳስበዋል።

Read More »
News

በ27 ከተሞች ከ1መቶ ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ …

በ27 ከተሞች ከ1መቶ ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የፕሮግራም ማሻሻያ ይፋ ሆነ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የወጣቶች የሥራ ልምምድ ፕሮግራም በሆነው «ብቃት» እና «የሥራ ማዕከላት አገልግሎት ማሻሻያ » ፕሮግራሞችን በአዳዲስ ከተሞች ለማስፋት የሚያስችል የማብሰሪያ መድረክ አካሂዷል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ የሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፣ ከ18-25 የሆኑና የትምህርት ደረጃቸው 12ኛ ክፍልና ከዚያ በታች የሆኑ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን ሕይወት በመለወጥ ረገድ የ«ብቃት» ፕሮግራም ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል፡፡
እስካሁን 93 ሺህ 665 የሚሆኑ ወጣቶች የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ያገኙ ሲሆን 54 ሺህ 913 ወጣቶች ደግሞ የስድስት ወር የተግባር ልምምዳቸውን አጠናቀዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ 52 ሺህ 786 የሚሆኑት ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ከተጠቃሚዎቹ መካከልም 67.6 በመቶ ያህሉ ወጣት ሴቶች መሆናቸው ፕሮግራሙ ማኅበራዊ ፍትሐዊነትን በግልፅ ያመላከተ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል “የሥራ ማዕከላት አገልግሎት ማሻሻያ” ፕሮግራም ባለፉት ዓመታት በአምስት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ 18 የሥራ ማዕከላት ዕድሳት ተደርጎላቸው የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ የተሟላላቸው ሲሆን አገልግሎታቸውንም ከኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ጋር የማቀናጀት ሰፊ ሥራ ተከናውኗል፡፡
ከዓለም ባንክ በተገኘ የ52 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ፋይናንስ የ«ብቃት» ፕሮግራም ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥር ከ11 ወደ 27 ለማስደግ መቻሉን፣ ብሎም በሚቀጥሉት 2 ዓመታት ውስጥም ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 29 የሆኑ 100,000 አዳዲስ ወጣቶች ተጠቃሚ እምደሚሆኑ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ይፋ አድርገዋል፡፡
ወደ ፕሮግራሙ አዲስ ከሚገቡት 16 ከተሞች መካከል ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ቢሾፍቱ፣ አሰላ፣ አምቦ፣ ነቀምት፣ አርባ ምንጭ፣ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ብርሃን፣ ሽሬ እንዳሥላሴ፣ ጅጅጋ እና ሐረር እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በ«የሥራ ማዕከላት አገልግሎት ማሻሻያ»ፕሮግራም አማካኝነት በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 88 የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት በሚተገበርባቸው ከተሞች ውስጥ ተጨማሪ 200 የሥራ ማዕከላት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ያገኛሉ።
እነዚህ ማዕከላት የቢሮ መገልገያ መሣሪያዎች ተሟልተውላቸው አገልግሎታቸው ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ የሚደረግ ሲሆን የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትንም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል፤
አዳዲስ ወደ ፕሮግራሙ የሚገቡ ከተሞች ከነባሮቹ ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ፤ እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮች፣ ከንቲባዎችና ባለድርሻ አካላት ለፕሮግራሞቹ ውጤታማነት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

Read More »
News

ለኢትዮጵያ ስታርትአፖች የዓለም አቀፍ ፋይናንስና የገበያ ዕድሎችን…

ለኢትዮጵያ ስታርትአፖች የዓለም አቀፍ ፋይናንስና የገበያ ዕድሎችን የሚያሰፋ የአጋርነት ስምምነት
የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) በአገር ውስጥ ያሉ ስታርትአፖችን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን እንዲሁም በፈጠራ ላይ የተመሰረቱ የንግድ ተቋማትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ የአጋርነት ስምምነት በኖርዌይ መቀመጫነቱን ካደረገው ዩሮኖርዲክ ፈንዲንግ አሊያንስ (ENFA) ጋር ተፈራረመ።

ይህ አጋርነት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተገነባ ያለውን የሥራ ፈጠራና የስታርትአፕ ሥነ-ምህዳር ይበልጥ ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ለአገር ውስጥ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የገበያ በሮችን የሚከፍት መሆኑ ተገልጿል።

‎በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት የአገር ውስጥ ስታርትአፖች በቀላሉ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፎችን፣ የተቀላቀሉ ፋይናንሶችን (Blended Finance) እና የግል ኢንቨስትመንቶችን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ስታርትአፖች አቅማቸውን በማሳደግ ምርትና አገልግሎታቸውን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በተለይም ወደ አውሮፓ፣ ወደ ኖርዲክ አገራት፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ (MENA) ቀጠናዎች እንዲያስፋፉ ስትራቴጂካዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
‎ትብብሩ የሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ለመገንባት የሚያግዙ ልዩ ሥልጠናዎችንና የምክር (Coaching) አገልግሎቶችን የሚያካትት ሲሆን፣ አገር በቀል ፈጠራዎች በዓለም አቀፍ ጥምረቶች ውስጥ እንዲሳተፉ ዕድል ይፈጥራል።
‎በዚህ ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ ስታርትአፖች እና የስነ-ምህዳሩ አንቀሳቃሾች የዩሮኖርዲክ ፈንዲንግ አሊያንስ (ENFA) የሚያቀርባቸውን ዘመናዊ ዲጂታል አገልግሎቶች በይፋ ማግኘት የሚችሉ ይሆናል።


‎ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የታገዙ የእርዳታና ፋይናንስ መፈለጊያ መሣሪያዎች፣ዓለም አቀፍ የኔትወርክና የትስስር መድረኮች፣የዓለም አቀፍ ፕሮጀክትና የገንዘብ መጠየቂያ ፕሮፖዛል ዝግጅት ድጋፎች፣ እንዲሁም
‎ከውጭ ኢንቨስተሮች ጋር በቀጥታ የሚያገናኙ የኢንቨስትመንት ትስስር (Matchmaking) ዕድሎች ከአገልግሎቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የተቋማቱ ተወካዮች በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ፈጠራና የቴክኖሎጂ አድማስን ለማስፋት ዓለም አቀፍ ትብብር ማድረጉ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይህ ተነሳሽነት የአገር ውስጥ ሥራ ፈጣሪዎች አስፈላጊውን ስትራቴጂካዊ ሀብትና ዕውቀት አግኝተው በዓለም መድረክ ላይ ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በቀጥታ ያግዛል።
ዩሮኖርዲክ ፈንዲንግ አሊያንስ (ENFA) ከ20 በላይ አገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፋይናንስ ድርጅቶችን፣ የባለሙያ ተቋማትን እና የፈጠራ አጋሮችን በአንድ ላይ ያቀፈ ትልቅ ዓለም አቀፍ ጥምረት ሲሆን፤ ይህ ስምምነት የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) በኢትዮጵያ ውስጥ ተንቀሳቃሽ፣ ዘመናዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገናኘ የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት የያዘውን አገራዊ ራዕይ የሚያፋጥን መሆኑ ታውቋል።
ዘገባው የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢኒስቲትዩት ነው;

Read More »
News

ኢንስቲትዩቱ ታላቅ ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤና የቴክኖሎጂ ውድድር ሊያካሂድ ነው

ኢንስቲትዩቱ ታላቅ ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤና የቴክኖሎጂ ውድድር ሊያካሂድ ነው
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት (FDRE TVTI) ከሰኔ 5 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚቆይ ታላቅ ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ እና የቴክኖሎጂ ውድድር እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብታሙ ሙሉጌታ ዛሬ ለተለያዩ ሚዲያ አካላት በሰጡት ጋዜጣዊ
የዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ በኢኒስቲትውቱ የምርምርና ቴክኖሎጂ ስራዎችን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ማሳደግ፣ የልምድ ልውውጥ ማካሄድ፣ እንዲሁም በተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎችና የልማት አጋሮች መካከል ያለውን ቅንጅትና አጋርነት ማጠናከር ነው።
ዘንድሮ የሚካሄደው ይህ ታላቅ ጉባኤ፦ “Future-Ready TVET and Technological Innovation for Sustainable Industrial Transformation” ወይም “መጻኢ የክህሎት ልማትና ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራን ያቀፈ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ እንዳለው ተገልጿል፡፡
ኮንፍረንሱ በዲጂታል ሽግግር እና የቴቬት ፈጠራኢንዱስትሪያል ለውጥ፣ በፈጠራ እና አረንጓዴ ሥርዓቶች፣በፖሊሲና አስተዳደር አካታችነት እና ዓለም አቀፍ አጋርነት ላይ አተኩሮ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡
በውድድሩ ላይ የሚቀርቡት የቴክኖሎጂ ስራዎችም በICT እና ዲጂታል ፈጠራ (AI, IoT, Cybersecurity)፣ በግብርናና አግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በላቀ ማኑፋክቸሪንግ፣ በታዳሽ ኃይልና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በግንባታና ዝቅተኛ ወጪ መኖሪያ ቤቶች ዘርፍ የተከፋፈሉ መሆናቸው ተገልጿል።
ላፉት ስድስት ወራት በተጠናከረ ሁኔታ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው ይህ ኮንፈረንስ እጅግ ሰፊ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከጀርመን፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ማላዊ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጨምሮ ከ16 አገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎችና ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል።
በጉባኤው ላይ ከ90 በላይ የምርምር ጽሑፎች እና ከ100 በላይ የቴክኖሎጂ/ፈጠራ ፕሮጀክቶች ከተመራማሪዎችና ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በጥብቅ የሳይንሳዊ ግምገማ ሂደት ያለፉ 30 ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የምርምር ጽሑፎች እና 34 የተመረጡ የቴክኖሎጂ ስራዎች ለቀራቢነትና ለውድድር በብቃት ማለፋቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ ኢንዱስትሪዎች፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የፈጠራ ባለቤቶች እና ፖሊሲ አውጪዎች በጋራ ይሳተፋሉ።

Read More »
News

የትምህርት ሥርዓትን ከገበያ ፍላጎት ጋር ማጣጣም

የትምህርት ሥርዓትን ከገበያ ፍላጎት ጋር ማጣጣም ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ነው
የትምህርት ሥርዓትን ከገበያ ፍላጎት ጋር ማጣጣም ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ አሚና መሐመድ ገለጹ።
በሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የአፍሪካ ዴቨሎፕመንት ኢምፓክት ፎረም 2026 በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) መካሄድ ጀምሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ አሚና መሐመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ ታላላቅ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች ባሉበት ወሳኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡
በዚህ ወቅት ጥራትና ዘላቂነት ያላቸው የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓቶችን ከገበያው ትክክለኛ ፍላጎት ጋር ማጣጣም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአፍሪካ ወጣት ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥራት ያላቸው የሥራ ዕድሎችን መፍጠር አፋጣኝ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባለፉት ዓመታት ከአምራች ኢንዱስትሪ መስፋፋት እስከ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና የክህሎት ልማት ያሉ የአፍሪካን አንገብጋቢ ተግዳሮቶች ለመፍታት ከመንግሥታት፣ ከቀጣናዊ ተቋማትና ከግል ዘርፉ ጋር በጋራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከዚህ የጋራ ሥራም ትልቅ ትምህርት መገኘቱን ጠቅሰው፣ምርምር፣መረጃና ማስረጃዎች ብቻቸውን ለውጥ አያመጡም፤ ከንግግርና ከሪፖርት ባለፈም ወደ ተግባራዊ እርምጃ መግባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።
የስራ ዕድሎችን መፍጠር በመንግሥታት ብቻ ሊሳካ እንደማይችል ጠቁመው፤ይህም የፖሊሲ አውጪዎችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የልማት አጋሮችንና የግል ዘርፉን በአንድ ላይ የሚያገናኝ ንቁ ሥነ-ምሕዳርን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
የዘንድሮው ፎረም መፍትሔዎችን ለመለየት፣ጠንካራ አጋርነትን ለመገንባትና ተግባራዊ የመድረሻ መንገዶችን ለመንደፍ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በአንድ ላይ ያገናኘ ሲሆን፣ከውይይት ባለፈ በመላው አፍሪካ ላሉ ወጣቶች ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩ ትርጉም ያላቸው ተግባራት እንደሚጠበቁበት ተመላክቷል። መረጃው የኢዜአ ነው። See less

Read More »
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
somSOM
Scroll to Top