Mols.gov.et

mols mols

News

በውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ላይ የተኮረ ውይይት ተካሄደ

በውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ላይ የተኮረ ውይይት ተካሄደ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀምና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የምክክር መድረክ ከውጭ ሀገር አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር አካሄደ፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፤ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት አዋጅን ወደ ሥራ ማስገባት ዋንኛው እንደሆነ በመጠቆም አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስችል መመሪያም በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የስልጠናና የምዘና ተቋማት አገልግሎትን ጨምሮ የመዳረሻ ሀገራት አሰራሮችን ማሻሻል፣ ለአቅም ግንባታ የሚረዱ ስልጠናዎችን መስጠትና ከኤጀንሲዎች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ የምክክር መድረኮችን ማካሄድ በልዩ ትኩረት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል እንደሚጠቀሱ ተብራርቷል፡፡
በነበሩት የተቀናጁ ጥረቶች በበጀት ዓመቱ ከ630 ሺህ በላይ ዜጎችን ከውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመትም የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል በስፋት የመላክ ዕቅድ መያዙን የገለፁት ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ህገወጥ አሰራሮችን ለማስወገድ በትኩረት እንደሚሰራም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ተገቢውን የገበያ ጥናት በማካሄድ የመዳረሻ ሀገራትን ማስፋት፣የአሰራር ችግሮችን በጥናት በመለየት ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጡ ሥርዓቶችን መዘርጋት ዘርፉ ምቹና ውጤታማ ሥነ ምህዳር እንዲኖረው ለማስቻል የተቀመጡ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የውጭ ሀገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የዜጎችንና የሀገርን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸውን ጉልህ ድርሻ ተገንዝበው ሥራውን በኃላፊነትና በታማኝነት መፈፀም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
አክለውም በኤጀንሲዎች መካከል የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት መፍታት፣ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ህገወጥ አሰራሮችን በጋራ መታገል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

Read More »
News

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የብየዳ ኢንስቲትዩት (IIW) …

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የብየዳ ኢንስቲትዩት (IIW) የ2026 ይፋዊ የአባልነት ሰርተፊኬት ተረከበች
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የብየዳ ኢንስቲትዩት (International Institute of Welding–IIW) 79ኛ ዓመታዊ ጉባኤ በቦርድ አባላት በሙሉ ድምፅ ከጸደቀች በኋላ፣ የ2026 ይፋዊ የአባልነት ሰርተፊኬቷን በይፋ ተረክባለች።
ኢትዮጵያን በዚህ ዓለም አቀፍ ተቋም የሚወክለው የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የብየዳ ልህቀት ማዕከል ነው።
ይህ አባልነት ኢትዮጵያ በብየዳ ቴክኖሎጂ፣ በክህሎት ልማት እና በዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትብብር ውስጥ እያሳየች ያለችውን እድገት የሚያረጋግጥ ታላቅ ዓለም አቀፍ እውቅና ነው።
የIIW የአስተዳደር፣ ኮሙኒኬሽን እና ሁነቶች ኃላፊ ሮሳሪያ ሩሶ (Rosario Russo) በላኩት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት፣ ኢትዮጵያን ወደ IIW ቤተሰብ በመቀላቀሏ ያላቸውን ደስታ ገልጸው፣ ይህ አባልነት የዕውቀት ልውውጥን ለማጠናከር፣ የሙያ ብቃትን ለማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ የሙያ ትስስርን ለማስፋት እና የጋራ ምርምርና ፈጠራን ለማበረታታት አስፈላጊ መሠረት እንደሚሆን ማስታወቃቸውን ከኢኒስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለኢትዮጵያ ይህ ስኬት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የብየዳ ስልጠና፣ የብቃት ማረጋገጫ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማጠናከር አዲስ እድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለማኑፋክቸሪንግ እና ለሌሎች የምርት ዘርፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የብየዳ ልህቀት ማዕከል በዘርፉ በሀገር ደረጃ ብቸኛ የልህቀት ማዕከል ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

Read More »
News

የሚተገበሩ አሠራሮችን ውጤታማ ለማድረግ …

የሚተገበሩ አሠራሮችን ውጤታማ ለማድረግ በፖሊሲ ንድፍና በተግባራዊ አፈጻጸም መካከል ያለውን ክፍተት መሙላት ወሳኝ መሆኑን ተመላከተ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ፐብሊክ ሴክተር ኢኖቬሽን ላብ (PSI Lab) ከአሜሪካ ኤምባሲ እና ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረክ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
የሥልጠናው ዋና ዓላማ ሚኒስቴሩ የዘርፉ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር ታግዞ ለመፍታት ያቋቋመውን የፒኤስ አይ ላብን(PSI Lab) የውስጥ አቅም ማጠናከር፣ ተቋሙ ያቀዳቸውን ስትራቴጂካዊ ግቦች ማሳካትና ማዕከሉን ከምርምር ተቋማት ጋር ማስተሳሰር ነው ተብሏል።
በዚህ መድረክ ላይ ከ8ቱ የኢትዮጵያ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችና ከ2ቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የአመራር አካላት እንዲሁም ከሚኒስቴሩና ከፒኤስአይ ላብ የተወጣጡ ሠራተኞችና አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካይ ዶ/ር ጆን ኬለር ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኤምባሲው ባለፉት ሦስት ዓመታት 10 የሀገሪቱን የሕዝብ ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ-ገዝነት ለሚያደርጉት የሽግግር ጉዞ የፖሊሲ ሰነዶችን በማስተካከልና የአመራር አቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናው ዩኒቨርሲቲዎች ካጋጠሟቸው ተግዳሮቶችና ስጋቶች በመነሳት፣ ከፖሊሲ ቀረጻ ባለፈ ወደ ትግበራ መሸጋገር የሚችሉበትን ክህሎት ለማስታጠቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው ኃላፊነትን ወደታች ለማውረድና (Decentralized) የሚተገበሩ አሠራሮችን ውጤታማ ለማድረግ በፖሊሲ ንድፍና በተግባራዊ አፈጻጸም መካከል ያለውን ክፍተት መሙላት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን(ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም ከፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ጋር የተከናወኑ ሥራዎች በከፍተኛ አመራሩ ባበለቤትነት ስለተመሩ የሚታይ ውጤት ማስመዝገብ መገመራቸውን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች በተግባራዊ ምርምር ስራዎቻቸው ማኅበረሰቡንና አካባቢውን ለመለወጥ ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው ተቋማት በመሆናቸው፣ ከድህነት መውጫና ወደ ብልጽግና መሸጋገሪያ መሰላል የመሆን ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዶ/ር ሀሰን አክለውም፤ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከመንግሥት በጀት የማይቀበል፣ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ግን ሙሉ በሙሉ የመንግሥት የሆነ ራሱን የቻለ (Autonomous) ተቋም መሆኑን በመጥቀስ፣ ተሳታፊዎች ከዚህ ስኬታማ ተሞክሮ ተቋማዊ ትምህርት መቅሰም እንደሚችሉ አብራርተዋል
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የፒኤስ አይ ላብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጥላሁን በጅቷል በበኩላቸው፤ ሥልጠናው በሲስተም ቲንኪንግ (Systems Thinking)፣ ዲዛይን ቲንኪንግ (Design Thinking)፣ ቼንጅ ማኔጅመንት (Change Management)፣ ትራንስፎርሜሽን (Transformation) እና ስትራቴጂክ ቲንኪንግ (Strategic Thinking) ዙሪያ ላይ ያተኮረ መሆኑን አብራርተዋል።
በአለም አቀፍ አሰልጣኞች ድጋፍ የሚሰጠው ይህ ስልጠና የሚከታተሉ ሰልጣኞች ሥልጠናውን ሲያጠናቅቁ በየተቋማቸው የሚተገብሯቸውን የስትራቴጂክ ዕቅዶችና የተለያዩ የስትራቴጂካዊ ፕሮፖዛሎችን ያዘጋጃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Read More »
News

የሥራ ዕድል ፈጠራን ወደ ሀብት ማፍሪያነት

‹‹የሥራ ዕድል ፈጠራን ወደ ሀብት ማፍሪያነት፣ ማኅበራዊ ተቋማትን ደግሞ ወደ ልማት ሞተርነት ለመቀየር የሁሉንም የዘርፉን አስፈፃሚ አካላት ቁርጠኝነትና ትጋት ይጠይቃል››
ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ
የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ የ2018 ዓመት አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከክልሎች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የዘርፉን አዲስ እሳቤ መነሻ በማድረግ ለዘመናት የተጠራቀመውን ዕዳ የሚያቃልሉ፣ የዜጎችን አሁናዊ ፍላጎት የዋጁና የመጪውን ዓለም ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረጉ ተግባራት በበጀት ዓመቱ መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህም መካከል “ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ” ቀዳሚው መሆኑን ጠቅሰው ሥራ ፈላጊዎች በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ልል ክህሎት (Soft Skills) እና ጠጣር ክህሎት (Hard Skills) ታጥቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቤተሰብ ቢዝነስን በማስፋፋት፣ እሴት አካይ ምርትን በማሳደግ እንዲሁም የመስሪያ፣ የመሸጫና የካፒታል አቅርቦት ችግሮችን በማቃለል ከከ4.9 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከአዳዲስ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
በኢኖቬሽን ላይ የተመሠረተ ስልት በመቀየስ ፈጣን የማደግ አቅም ያላቸውን ኢንተርፕራይዞች በቅርበት በመደገፍ ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ መቻሉን የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ለመሰል ኢንተርፕራይዞች የተሰጠው ልዩ ትኩረት “ከዳቦ በላይ” የሚለውን አዲስ እሳቤ ለማሳካት ዋነኛ ስልት ሆኖ መገኘቱንም አመላክተዋል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራን ወደ ሀብት ማፍሪያነት፣ ማኅበራዊ ተቋማትን ደግሞ ወደ ልማት ሞተርነት ለመቀየር የሁሉንም የዘርፉን አስፈፃሚ አካላት ቁርጠኝነትና ትጋት እንደሚጠይቅም በአፅንኦት አንስተዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ዘርፍ የሀገራችንን ወደ ላቀ ብልጽግና ለማሸጋገር ያለውን አስተዋፅኦ በሚገባ በመገንዘብ የዘርፉን ተልዕኮዎች በክህሎትና ኢኖቬሽን ለመምራት ሁሉም አስፈፃሚ አካላት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ክቡር አቶ ሰለሞን በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ አሳስበዋል፡፡

Read More »
News

የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ

የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በተከናወኑ ተግባራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ አምራች ኃይልነት መቀየር ተችሏል
ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የሚተገበረውን “የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ” ፕሮግራም በላቀ ጥራትና ተጠያቂነት ለመተግበር የሚያስችል የማስፈጸሚያ መመሪያ ሥልጠና በይፋ ተጀመረ።
የሥልጠና መድረኩን በይፋ የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሥራ፣ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታከናውናቸው ታሪካዊና መዋቅራዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሪፎርሞች ዋና ማዕከል ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ” መሆኑን ጠቀሰው የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በተከናወኑ ተግባራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ አምራች ኃይልነት እየተቀየሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
መንግስት በመደበኝነት ከሚያከናውናቸው የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች ጎን ለጎን ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመተባበር እየተገበራቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶችም ለወጣቶች ሰፊ የሥራ መፍጠሪያ አማራጭ በመሆን እያገለገሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በዚሁ መሰረት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በሚተገብረው ‹‹የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ›› ፕሮግራም በሦስቱ ዙር 54,913 ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ እንዲሁም 52,786 ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡
የተገኘው ውጤት የመንግሥት የሥራ ዕድል ፈጠራ ፖሊሲ በተግባር በዜጎች ሕይወት ላይ የሚታይና የሚዳሰስ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የሚያሳይ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ጥራቱ በየነ የሥራ ዕድል ፈጠራ ለከተሞች ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው ‹‹የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም›› መተግበር ከጀመረ በኋላ ወደ ከተሞች የሚደረግ ፍልሰትን ጨምሮ በተለያ ምክንያቶች ለሥራ አጥነት ችግር የተጋለጡ ወጣቶችን ህይወት በእጅጉ መቀየር እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከፍያለው ከበደ በበኩላቸው በክልሉ በፕሮግራሙ ከስምንት መቶ በላይ ወጣቶችን በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ተሳታፊዎች ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ ብቁ የሆኑ አለማማጅ ድርጅቶችን መለየት እና መመልመል፣ የሥልጠናና የሙያ መስኮችን በጥናት መወሰን፣ተጠቃሚ ወጣቶችን በግልጽነትና በአድልዎ አልባነት መመዝገብ፣ የቴክኒክና ሙያ (TVET) ተቋማትንና የግሉን ዘርፍ በተቀናጀ መልኩ ማስተሳሰርና የከተማ አመራርን በሙሉ የሚያሳትፍ የኦሪየንቴሽን መድረክ በአጭር ጊዜ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውም ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

Read More »
News

ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ…

ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የማስተባበርና የመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት አደረጃጀት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሴት ሠራተኞች ፎረም አባላት በፎረሙ መተዳደሪያ ደንብ እና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያዩ፡፡
በዋናነት ሴቶች እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ፣ አቅማቸውን እንዲገነቡ እና በሥርዓተ ፆታ እኩልነት ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱን መቋቋም ተከትሎ ፎረሙ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ እምዬ ቢተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ፎረም የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሠራ መሆኑን ገልፀው በሥራ ቦታ ላይ የሴቶች መብትና ክብር በአግባቡ ተጠብቆ መሰራቱን በቅርበት የሚከታተል ቁልፍ አደረጃጀት ነው ብለዋል፡፡
ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የማስተባበርና የመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር በሚገኙ ሦስቱም ዘርፎች ማለትም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎት ልማትና በሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ውስጥ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፎረሙ መመሥረት ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የሴቶችን አቅም ማሳደግ፣ የሚደርሱ ጥቃቶችንና በደሎችን በጋራ መከላከል እንዲሁም ልምድና ተሞክሮዎችን መለዋወጥ የፎረሙ ዝርዝር ዓላማዎች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡
አደረጃጀቱን ይበልጥ የማጠናከር ሥራ ከሁሉም አባላት እንደሚጠበቅ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን ተሳታፊዎቹ በቀረቡት የመተዳደሪያ ደንብና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በጥልቀት መክረውና በሙሉ ድምጽ አፅድቀው ውይይቱን አጠናቀዋል፡፡

Read More »
News

መንግሥት ለጀመረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ኢንተርፕራይዞች .

‹‹መንግሥት ለጀመረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንትና ዋና ሞተሮች ናቸው ››
ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ፣ የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ፣ ሚኒስትር ዴኤታ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለዘርፉ አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፖሊሲ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡
የስልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰሎሞን ሶካ፤ መንግሥት ለጀመረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንትና ዋና ሞተሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞች ይህን ወሳኝ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የተቀረፀው የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፖሊሲ የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመቅረፍ ፣ ዕድገትን ለማስቀጠልና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቁልፍ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዘርፉ የነበሩ ድጋፎች የተበጣጠሱና አካታች ባለመሆናቸው ኢንተርፕራይዞች በአንድ ደረጃ ላይ ተንጠልጥለው እንዲቀሩ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ አዲሱ ፖሊሲ እነዚህን ማነቆዎች በዘላቂነት ለመፍታት የተዘጋጀ ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንተርፕራይዞች በሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ላይ ዋንኛ ተዋናይ ወደሚሆኑበት ደረጃ እንዲሻገሩ የተፈጠረውን ምቹ የፖሊሲ አውድ በመጠቀም ለተግባራዊነቱ እያንዳንዱ የዘርፉ አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ርብርብ እንዲያደርጉ ክቡር አቶ ሰለሞን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ የሚተገበረው ‹‹ በግብርና ኢንተርፕራይዞች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክት የፖሊሲውን ሰነድ በማሳተም፣ በማሰራጨትና የግንዛቤ መስጨበጫ መድረኩን በማዘጋጀት ላበረከተው የላቀ አስተዋጽዖም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

Read More »
News

በጋራ እንፈጥራለን

በጋራ እንፈጥራለን
የሥራና ክህሎት ሚንስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የሚያዘጋጀው የቴክኖሎጂ ባህል ግንባታ ፓነል ውይይት ለአምስተኛ ዙር «በጋራ እንፈጥራለን» በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጸዳለ ተክሉ እንደገለጹት፤ ይህ የፓናል ውይይት በቡድን ስራ ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ምክረ-ሀሳብ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
ስለ ኢኖቬሽንና ፈጠራ ሲነሳ የቡድን ስራ ወሳኝ ተግባር መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ኢንስቲትዩቱ ለፈጠራ ባለሙያዎች አርአያ እንዲሆን የተለያዩ ዘርፎች እርስበርስ መተሳሰር እንዳለባቸውና በዘርፉ ያሉ በርካታ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ለማሳካት የቡድን ስራ የግድ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በጋራ መስራት እውቀትን፣ ክህሎትን እና ችሎታን በማቀናጀት የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ግኝቶችን ለመፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል።
በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ላይ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑት ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የዕለቱ የፓናል ውይይት ዋና ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን በጋራ መስራታቸው ለፈጠራ ስራቸው ያበረከተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለታዳሚ ወጣቶች ልምዳቸውን አካፍለዋል።
ወጣቶቹ ሀመረ፣ ሩት፣ ያብስራ እና ሪሃና “የተንቀሳቃሽ የአእምሮ ግፊት መከላከያ መሳሪያ” ላይ ያመጡትን አዲስ የፈጠራ ስራ በሂደቱ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች እና በጋራ ያሳለፉትን ጠንካራ ተሞክሮ አቅርበዋል።
እነዚህ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ወደፊትም ፕሮጀክታቸውን ይበልጥ በማሳደግ ወደ ምርት ለማሸጋገር እና ለሀገራችን የጤና ዘርፍ ትልቅ መፍትሄ ለማምጣት በርትተው እንደሚሰሩ በቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በኢንስቲትዩቱ የሊደርሽፕና ማኔጅመንት ፋኩልቲ አማካኝነት በቡድን ስራ ውጤታማነት፣ ተግዳሮቶች እና ሊከተሏቸው በሚገቡ ስልታዊ አካሄዶች ላይ ያተኮረ መወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በቡድን መስራት በዘላቂነት ትርፋማ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን ከታዳሚዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በአጠቃላይ በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ባህልን ለማስረጽ የተጀመረው ይህ የፓነል ውይይት መድረክ በየጊዜው ሰፊና በጎ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች እየተገኙበት መሆኑ ተመላክቷል።
መረጃው የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢኒስቲትዩት ነው፡፡

Read More »
News

ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር..

ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በለውጡ መንግሥት የተተገበሩ የሪፎርም ሥራዎች የወጣቶችን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተጨባጭ ውጤቶችን አስገኝተዋል።
ባለፉት 4 ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ለ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠራቸውን ጠቁመው፣ ከዚህም መካከል 75 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለውጡ ካስገኛቸው ዋና ዋና ስኬቶች መካከል ወጣቶች ከተለመደው የቅጥር ሐሳብ ወጥተው ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩና ለሌሎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፈጠራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የቤተሰብ የንግድ ሥራዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አክለዋል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች መስፋፋትና ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ለወጣቶች ዘመናዊ፣ ፈጣንና ምቹ የሥራ ዕድሎችን የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ የዲጂታል የሥራ ገበያ ላይ የሀገሪቱንና የወጣቶቹን ተወዳዳሪነት ማሳደጉን አብራርተዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ በበኩላቸው፤ ከለውጡ በኋላ የወጣቶችን አቅም በማሳደግ ረገድ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ተስፋ ሰጪ፣ ዘላቂና ክህሎት መር የሥራ ዕድሎችን በተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ትልቅ አቅም መገንባቱን አብራርተዋል።
በመዲናዋ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት ጋሻው ዓለሙ የመኪና ጎማና ባትሪዎችን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ ላይ መሰማራቱን ጠቅሷል፡፡
የምናመርታቸው ምርቶች የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስና ቆሻሻን ወደ ሀብት ከመቀየር ባለፈ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን የሚያሳድጉና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብሏል።
በማኅበር በመደራጀት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ የቤትና የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችን እያመረቱ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ ወጣት አስቻለው ጌትዬ ነው፡፡
በቀጣይም የምርቶቻቸውን የገበያ ተደራሽነትና የሥራ ዕድሎችን ይበልጥ ለማስፋፋት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግሯል። መረጃው የኢዜአ ነው።

Read More »
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
somSOM
Scroll to Top