Mols.gov.et

ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ…

July 3, 2026
ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የማስተባበርና የመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት አደረጃጀት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሴት ሠራተኞች ፎረም አባላት በፎረሙ መተዳደሪያ ደንብ እና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያዩ፡፡ በዋናነት ሴቶች እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ፣ አቅማቸውን እንዲገነቡ እና በሥርዓተ ፆታ እኩልነት ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱን መቋቋም ተከትሎ ፎረሙ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ እምዬ ቢተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ፎረም የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሠራ መሆኑን ገልፀው በሥራ ቦታ ላይ የሴቶች መብትና ክብር በአግባቡ ተጠብቆ መሰራቱን በቅርበት የሚከታተል ቁልፍ አደረጃጀት ነው ብለዋል፡፡ ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የማስተባበርና የመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር በሚገኙ ሦስቱም ዘርፎች ማለትም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎት ልማትና በሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ውስጥ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፎረሙ መመሥረት ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የሴቶችን አቅም ማሳደግ፣ የሚደርሱ ጥቃቶችንና በደሎችን በጋራ መከላከል እንዲሁም ልምድና ተሞክሮዎችን መለዋወጥ የፎረሙ ዝርዝር ዓላማዎች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ አደረጃጀቱን ይበልጥ የማጠናከር ሥራ ከሁሉም አባላት እንደሚጠበቅ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን ተሳታፊዎቹ በቀረቡት የመተዳደሪያ ደንብና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በጥልቀት መክረውና በሙሉ ድምጽ አፅድቀው ውይይቱን አጠናቀዋል፡፡
somSOM
Scroll to Top