Mols.gov.et

News

News

በ47ኛው የዓለም የክህሎት ውድድር ተሳትፎ ላደረገው የልዑካን ቡድን እውቅና ተሰጠ

በ47ኛው የዓለም የክህሎት ውድድር ተሳትፎ ላደረገው የልዑካን ቡድን እውቅና ተሰጠ
በአዲሱ ዓመት መባቻ ላይ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንሳይ ሊዮን በተካሄደው ዓለም አቀፉ የክህሎት ውድድር ተሳትፋለች፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ በሦስት የሙያ መስኮች ተወዳዳሪዎችን አሳትፋለች፡፡
በዚህም በICT and Networking ጽዮን አዳነ፣ በCNC Machine የሮም ነሽ አዋሬ እና በFurniture Making ብሩክ ፀጋዬ ሀገራችንን ወክለው ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
በICT and Networking ተወዳዳሪ የነበረችው ፅዮን አዳነ በመድረኩ “Best of Nation recognition” ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች፡፡
ከመድረኩ ተሳትፎ በርካታ ልምዶችን ማግኘት እንደተቻለ የተጠቆመ ሲሆን ለተሳታፊዎች፣ የልዑኩ ቡድን አስተባባሪዎች እና ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ክህሎት ማህበረሰብ አባል ሀገር እንድትሆን ጥረት ላደረጉ አመራሮች ከክብርት ሚኒስቴር የምስጋና እና የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡

Read More »
News

ዲጂታላይዜሽን ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ልህቀት

ዲጂታላይዜሽን ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ልህቀት
በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የዲጂታላይዜሽን ትግበራ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ሀገራችን በ2025 ዓ.ም ዲጂታል ኢኮኖሚን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚስችል ዕቅድ መያዟን አስታውሰው የዕቅዱ ውጤታማነት እያንዳንዱ ዘርፍ ዲጂታላይዜሽንን ለማስፋፋት በሚያደረገው ጥረት ይወሰናል ብለዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሁሉም ዘርፎች የሚያስፈፅማቸውን ተልዕኮዎች በራስ አቅም በለማው የዲጂታል ሥርዓት አማካኝነት እያስተገበረ እንደሚገኝ የገለፁት ክቡር ዶ/ር ተሻለ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በተለያዩ የፖሊቴክኒክ ኮሌጆች የዲጂታል መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የይዘት ዝግጅትና የሰው ኃይል ልማት ሥራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በቅርቡ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኝ መምህራን በሰጠው ስልጠና ላይ ዲጂታላይዜሽን አንዱ የትኩረት መስክ እንደነበር ያስታወሱት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ክልሎችም አሰልጣኝ መምህራንንም ሆነ የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን ለዲጂታላይዜሽን ዘመን ዝግጁ ማድረግ እና ከፖሊቴክኒክ በታች ያሉ ኮሌጆችን በዲጂታላይዜሽን መሰረተ ልማት በማጠናከር ሥራ ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ዲጂታላይዜሽን ለማስተግበር የተዘጋጀው ስትራቴጂ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Read More »
News

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ጋር ተወያዩ

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ጋር ተወያዩ
በውይይቱ የሥራ ፈጠራ ስነ-ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ መንገስት እያደረገ ስላለው ጥረትና ሚኒስቴሩ እያከናወነ ስላለው ሥራ ክብርት ሚኒስትር ገለፃ አድርገዋል፡፡
በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታትና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሥራ ፈጠራን ለማበረታታት ከሁሉም ባለድርሻ እና አጋር አካት ጋር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ክብርት ሚኒስትር ጠቁመዋል፡፡
ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት ማህበሩ የጀመረውን ሥራ ያደነቁት ክብርት ሚኒስትር በቀጣይ ሚኒስቴሩ በሥራ ፈጠራው መስክ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከማህበሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የማህበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር የማህበሩን የቀጣይ ዓመታት ስትራቴጂክ ሰነድ (EYEA 2027) ለክብርት ሚኒስትር አስረክበዋል፡፡

Read More »
News

በልምድ ለተገኘ ሙያ እውቅና መሰጠቱ ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንዳሉት ተገለፀ

በልምድ ለተገኘ ሙያ እውቅና መሰጠቱ ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንዳሉት ተገለፀ
በልምድ የተገኘ ሙያን በምዘና በማረጋገጥ እውቅ መስጠት የሚያስችል መምሪያ ትላንት በአዲስ አበባ ይፋ ተደርጓል፡፡
ይህን ተከትሎ የዘርፉ አስፈፃሚ፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላት እንዲሁም የተለያዩ ድርጅት ተወካዮች ውይይት አካሂደዋል፡፡
በዚህም በልምድ ለተገኘ ሙያ እውቅና መሰጠቱ ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንዳሉት ነው የተገለጸው፡፡
በርካታ ዜጎች በመደበኛው የትምህርትና ስልጠና ስርዓት ሳያልፉ የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት ሆነው በሥራ ገበያውና በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንዳሉ ተመላክቷል፡፡
ይህ እውቅና እንዲያገኝ መደረጉ ባለሙያዎቹ እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ የሚያልቅ እንደሆነም ነው በመድረኩ ላይ የተነሳው፡፡
ስርዓቱ ባለሙያዎቹ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር የክህሎት ክፍተታቸው ተለይቶ እንዲሞላ፣ የሥራ ዕድልና ተጠቃሚነታቸው እንዲሰፋ፣ ሀገር በቀል ሙያዎች እንዲጎለብቱ እንዲሁም በልምድ ሙያ ያላቸውን ዜጎች ብቃታቸውን በማረጋገጥና ወደ መደበኛው ስርዓት በማስገባት የሥራ ገበያው ላይ ብቁና በቂ የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲኖር የሚያደርግ እንደሆንም ነው የተገለፀው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ ውይይቱን ሲያጠቃልሉ እንደገለጹት የፕሮግራሙ ይፋ መሆን በሀገራችን በመደበኛና በአጫጭር ስልጠና በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሲሰጥ ከቆየው ስልጠና በተጨማሪ ዜጎችን የክህሎት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል ዋንኛ አማራጭ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

Read More »
News

ማሳሰቢያ

ማሳሰቢያ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተግባራዊ እያደረገ ያለው የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት መነሻና መዳረሻው የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው፡፡
በዘርፉ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በተሰራው ጠንካራ የሪፎርም ሥራ በቴክኖሎጂ ጭምር በመታገዝ ህብረተሰቡን ካላስፈላጊ ወጪና እንግልት በመታደግ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ ሥራ አሁንም ተጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል፡፡
ነገር ግን ስምሪቱን በተመለከተ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ስምና አርማ እንዲሁም የከፍተኛ አመራሩን ስምና ምስል ጭምር በመጠቀም የተለያዩ ማስታወቂያዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሕገወጦች በመዘዋወር ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማስታወቂያዎች ሀሰተኛ መሆናቸው ታውቆ ሁሉም ላላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረግ ጥንቃቄ እንዲያደረግ እናሳስባለን፡፡
የሥራ ስምሪቱን በተመለከተ አዳዲስ ነገሮች ሲኖሩ የተቋማችንን ይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስርን ጨምሮ በሁሉም የሚደያ አማራጮች የምናሳውቅ ይሆናል፡፡
በሥራ ስምሪቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልግ ማንኛው ሰው በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ላይ (https://lmis.gov.et/auth) እንዲመዘገብ እና ህጋዊ አማራጮችን ብቻ በመጠቀም ደህንነቱ የተረጋገጠ የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በድጋሜ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

Read More »
News

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ክቡር ቼን ሃይ ጋር በቅንጅት መስራት በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ወይይት ተካሄደ፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ክቡር ቼን ሃይ ጋር በቅንጅት መስራት በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ወይይት ተካሄደ፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት ክብርት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት በቻይና እድገትና ልማት ውስጥ የቴክኒከና ሙያ ትልቅ አበርክቶ እንደነበረው እና ኢትዮጵያም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በያዘችው ጉዞ ዘርፉ የማይተካ ሚና እንዳለው ከግምት በማስገባት መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራው ያለውን ሥራ በዝርዝር ለአምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ቻይና ለኢትዮጵያ በዘርፉ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ክቡር አምባሳደሩ አረጋግጠውልኛል ብለዋል ፡፡
ከውይይቱ በኋላ በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በቻይና መንግስት ድጋፍ የተገነባውን የሉባን ወርክሾፕ የጎበኘን ሲሆን በቻይና መንግስት የትምህርት እድል ተሰጥቷቸው ስልጠናቸውን እየተከታተሉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በበይነ መረብ አግኝተው ማናገራቸውንና ማበራታታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ ግንኙነት ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር የቻይና አፍሪካን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድግ በመሆኑ በኢትዮጵያ የቻይና አምበሳደር ለክቡር ቼን ሃይ በትብብር አብሮ ለመስራት ላሳዩን ቁርጠኝነት ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

Read More »
News

የኮደርስ ስልጠና ዜጎች በዲጂታሉ ዓለም ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል- የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

የኮደርስ ስልጠና ዜጎች በዲጂታሉ ዓለም ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል- የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
”አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ መርኃ ግብር የዜጎችን አቅም በማሳደግ በዲጂታሉ ዓለም ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የ”አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ መርኃ ግብር በኢትዮጵያ መንግስትና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትብብር የተጀመረ የዲጂታል ሥራ ክህሎት ማሳደጊያ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ “ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ከዓለም ጋር ይፎካከር” በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣በአንድሮይድ ማበልፀግ ፣ በዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የ”አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ ኢኒሼቲቭ የዜጎችን የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት አቅም የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ዜጎች የዲጂታል ክህሎት በመጨበጥ ስራ እና ሀብትን በመፍጠር ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን የበለጠ የሚያግዝ እንደሆነ አስረድተዋል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶችን ከማፍራት አንጻር የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት የሚያልፉ ዜጎች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ከማብቃት በተጨማሪ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ማፍለቅ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።
ስልጠናው በሌላው ዓለም ያሉ ስራዎችን ባሉበት ሆነው መስራት እንዲችሉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የራሳቸውን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለሀገር ለማበርከት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ሲሉ አመላክተዋል።
ይህም የዜጎችን የተወዳዳሪነት አቅም በማሳደግ በዲጂታሉ ዓለም ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል ነው ያሉት።
መርኃ ግብሩ በፈረንጆቹ በ2026 አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታሳይንስና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት የሚያስጨብጥ ይሆናል።
#ኢዜአ
መስከረም 18/2017

Read More »
News

የጥራት ሥራ አመራርን በአግባቡ መተግበር የሪፎረም ሥራዎቻችንን ለማፅናት ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ

የጥራት ሥራ አመራርን በአግባቡ መተግበር የሪፎረም ሥራዎቻችንን ለማፅናት ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እየተገበረው በሚገኘው ISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር የኦዲት ግኝት ላይ ውይይት ተካሄዷል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ነቢሀ መሀመድ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት፣ ISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራርን ለመተግበር የሚያስችሉ ሥራዎች ደረጃ በደረጃ እየተከናወነ ቆይቷል፡፡
ይህን ተከትሎ በሙከራ ደረጃ በሚኒስቴር መ/ቤቱ እየተተገበረ የሚገኘውን ISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራርን ውጤታማነትን የሚመዝን የኦዲት ሥራ ተሰርቷል።
በኦዲት ግኝቶቹ መሰረት በቀጣይ በአስቸኳይ የማሻሻያና የእርምት እርምጃዎች ተወስደው ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባል ብለዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎችን እየተገበረ የሚገኝ ተቋም እንደመሆኑ እነዚህን የሪፎርም ሥራዎች ለማፅናት የጥራት ሥራ አመራርን በአግባቡ መተግበር ወሳኝ መሆኑንም አመላክተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር 20 ተቋማትን ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችን እንዲያሟሉ ዕቅድ ይዞ እየሰራ ቆይቷል፡፡
እስካሁን የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንዲሁም የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የISO 9001:2015 እንዲሁም የሀዋሳ ፖሊቴክኒከ ኮሌጅ የISO 21001:2018 የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አግኝተዋል፡፡

Read More »
News

የአሰልጣኞችን አቅም ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሰራ ተጠቆመ

የአሰልጣኞችን አቅም ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሰራ ተጠቆመ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቸ “ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት” በሚል የተሰጠውን ሀገር አቀፍ የቴክኒክና ሙያ አመራሮችና አሰልጣኞች ስልጠና አጠቃላይ ሂደት ገምግመዋል፡፡
በዘርፉ ፖሊሲና አዳዲስ እሳቤዎች ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤ መፍጠር እና የአሰልጣኞችን ባህሪያዊና ቴክኒካዊ ብቃትን ማሳደግ ታሳቢ ባደረገው በዚህ የስልጠና መድረክ በ19 የስልጠና ማዕከላት ከ20 ሺህ በላይ አሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡ ይህም ከዕቅዱ 86 በመቶ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
የሥልጠና መድረኩ ግቡን ያሳካና ለቀጣይ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በርካታ ልምዶች የተገኙበት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ እንደ ዘርፍ የተቀረጹ አዳዲስ እሳቤዎችንና ሰትራቴጂዎችን ወደ መሬት ለማውረድ የአሰልጣኞች ሚና የማይተካ ነው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ አሰልጣኞች በፖሊሲና ሰትራቴጂዎች ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤና ዝግጁነት እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር በዘርፉ መነቃቃትን መፍጠር ችሏል፡፡
በቀጣይ በተለያዩ ምክንያቶች ስልጠናውን መውሰድ ያልቻሉ አሰልጣኞችን ለመድረስ እንደሚሰራ የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር የአሰልጣኞቸ የአቅም ግንባታ መርሃ ግብሮች ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ለመድረኩ ስኬት አበርክቶ ለነበራቸው አስተባባሪዎች፣ የክልል አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ ከፍተኛ የትምህርትና የቴክኒክና ማሰልጠኛ ተቋማት አንዲሁም ለሁሉም ሰልጣኞች ክብርት ሚንስትር ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Read More »
News

የክህሎት ስልጠና ለወሰዱ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር …

የክህሎት ስልጠና ለወሰዱ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን የሲዳማ ክልል የሥራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ገለፀ፡፡
በቢሮው የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ም/ል ኃላፊ አቶ ካንቹላ ካንቤ እንደገለፁት ሥራ ፈላጊዎችን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኘው SHINTS ETP GARMENT PLC Ethiopia የተሰኘው ካምፓኒ ጋር በማስተሳሰር የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው ይገኛል፡፡
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና በሌሎችም አካባቢዎች የሥራ ልምድ ያላቸውን ብቁ ባለሙያዎች የመመዝገብና ከሐዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ብቃታቸውን የማስመዘን ሥራ በቢሮው እየተከናወነ እንደሚገኝም አቶ ካንቹላ ገልፀዋል፡፡
ቢሮው ከጋርመንት ፋብሪካው ጋር ከባለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ሲሠራ የቆየ ሲሆን በጋርመንት ዘርፍ ለሰለጠኑና ብቃታቸው በምዘና ለተረጋገጠ 1,217 ለሚሆኑ ባለሙያዎች በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ከቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡፡፡

Read More »
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
tigTIG
Scroll to Top