Mols.gov.et

News

News

16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አውደ-ርዕይና የፈጠራ ሥራዎች ውድድር ተጠናቀቀ

16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አውደ-ርዕይና የፈጠራ ሥራዎች ውድድር ተጠናቀቀ
ላለፉት ቀናት በአራዳ ፓርክ “የቴክኖሎጂ ልህቀት ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አውደ-ርዕይና የፈጠራ ሥራዎች ውድድር በደማቅ ሥነ-ስርዓት ተጠናቋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፤ የቴክኖሎጂ ታሪክ የኢኮኖሚ ልማት ታሪክ መሆኑን በጥልቀት በመተንተን፣ ባለፉት ቀናት የቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች የሀገሪቱን የልማት ተስፋና ተጨባጭ እንቅስቃሴ የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።
መንግስት የክህሎት መር የሥራ ስምሪትን እንደ ዋነኛ ፖሊሲ በመከተሉ፣ ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም በተግባር እንዲያሳዩና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ራሳቸውን በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነ-ምግባር በማነጽ ለሀገራቸው ብልጽግና እንዲተጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።
አክለውም፣ ወጣቶች የሥራን ክብር በመረዳትና ዲጂታል ክህሎታቸውን በማሳደግ የሀገር ግንባታ አካል እንዲሆኑና የጀመሩትን የፈጠራ ሥራ ወደ ቢዝነስ በመቀየር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁም አደራ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው አውደ-ርዕይ ቴክኖሎጂዎችን ለዕይታ ብቻ ከማቅረብ ባለፈ፣ በቀጥታ ወደ ፋብሪኬሽን ኢንጂነሪንግ በማሸጋገር ለተጠቃሚው ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ የተተገበረበት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የውጭ ምንዛሬን የሚያድኑ ተኪ ምርቶችን ማምረት እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጡበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዕለቱ በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በዲጂታል አይሲቲ ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ፣ በፋሽን ዲዛይን፣ በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ከፍተኛ ውጤት እንዲሁም በስፖርት ውድድር አሸናፊ በመሆን በደረጃ ለወጡ ተወዳዳሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
በመድረኩ የተጀመረው የቴክኖሎጂ ሽግግርና የምርት መተካት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን የቢሮው መረጃ ያመለክታል። ዘገባው የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ነው።

Read More »
News

ፈጠራና ፍጥነትን ማዕከል አድርጎ ተኪ ምርት ማምረት…

ፈጠራና ፍጥነትን ማዕከል አድርጎ ተኪ ምርት ማምረት ለኢኮኖሚ ሽግግሩ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
የሀገር ውስጥ ምርታማነትን በፈጠራና በፍጥነት በማሳደግ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የኢኮኖሚ እድገቱን ማፋጠን እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለጹ።
አፈ-ጉባኤዋ ይህንን የገለፁት በሸገር ከተማ ገላን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተጀመረውን የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የፈጠራና የክህሎት ውድድርን ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
የተከበሩ ወ/ሮ ሰዓዳ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፤ መንግስት በትምህርት፣ በሙያ ስልጠና እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎች ውጤት እያሳዩ ይገኛሉ።
በተለይም በየዓመቱ የሚፈጠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሥራ ባህልን በመቀየር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህ ፈጠራዎች የሥራ ዕድልና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የስልጠና ተቋማትም የገበያ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ጥናት በማድረግና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ያላቸውን ትብብር በማጠናከር፤ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት እንዳለባቸው ተገልጿል።
ይህም የኢኮኖሚ ሽግግሩን ከማሳለጡ ባለፈ ሀገር በቀል ዕውቀትን ወደ ምርት በመለወጥ ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል።
የኦሮሚያ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ጎልጋ በበኩላቸው፤ ቢሮው ሰፊ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንንም ግብ ለማሳካት ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የክህሎት ማዳበሪያና ዘላቂነት ያላቸው ስልጠናዎች በስፋት እየተሰጡ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በ22 ክላስተሮች እና በ215 የስልጠና ተቋማት መካከል የሚካሄደው ይህ ውድድር፤ የሸገር ከተማን የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ለተያዘው እቅድ ስኬት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በመድረኩ መገለፁን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Read More »
News

5ኛው ዙር ክልላዊ የቴክኖሎጂና ተግባራዊ ምርምር ውድድር ተጠናቀቀ

5ኛው ዙር ክልላዊ የቴክኖሎጂና ተግባራዊ ምርምር ውድድር ተጠናቀቀ
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሲያካሂድ የነበረው የ2018 በጀት ዓመት የ5ኛው ዙር ክልላዊ የቴክኖሎጂና ተግባራዊ የጥናትና ምርምር ውድድር ተጠናቋል፡፡
ውድድሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪና ከክልል መንግሥታት ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከርና የምርምር ውጤቶች በቀጥታ ወደ ማህበረሰቡ የሚወርዱበትን ዕድል ለመፍጠር ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሠረት አድርጎ የተካሄደ ነው፡፡
በዳኞች ግምገማና በድምር ውጤት መሠረት፣ የአሶሳ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እና የቡለን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በአንደኝነት በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያና የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የአሶሳ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ደግሞ የሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡
ቢሮው ለአሸናፊዎቹ እንደየደረጃቸው ከ15ሺህ እስከ 25ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ማበረታቻና የዕውቅና ምስክር ወረቀት በማበርከት ኮሌጆቹ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በጥናትና ምርምር ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ አበረታቷል፡፡
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሰላም ሸንገል በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፣ ቴክኖሎጂ ለሀገርና ለክልል ልማት የማይተካ ሚና አለው፡፡ እንዲህ ያሉ ውድድሮች በወጣቶችና በተመራማሪዎች ዘንድ የፈጠራ ባህልን ለማዳበር እና ተግባራዊ ምርምሮችን ወደ ምርታማነት ለመቀየር ወሳኝ መድረኮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን ይህን ውጤታማ ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው አረጋግጠዋል።
በተለይም አሶሳ ግብርና ኮሌጅ በአንደኝነት እንዲያሸንፍ ያስቻለው “Improving organic farming practice by using vertical farming” በሚል ርዕስ ያቀረበውና በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት ያለመው የምርምር ሥራ በዳኞች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል፡፡
ተመራማሪዎቹና የኮሌጁ አመራሮች በበኩላቸው የተገኙ ውጤቶችን ወደ ማህበረሰቡ የማሸጋገርና በሀገር አቀፍ ደረጃም የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ዘገባው የቤኒሽንጉል ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ነው

Read More »
News

ትውልዱ በቴክኒክና ሙያ. . .

ትውልዱ በቴክኒክና ሙያ ያገኘውን ክህሎት ለእድገት በተግባር መተርጎም ይጠበቅበታል
ትውልዱ በቴክኒክና ሙያ መስክ የሚያገኛቸውን ክህሎቶች በተግባር በመተርጎም ለእድገት የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ገለጸ።
የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ100ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት “ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አከብሯል።
በሥነ-ሥርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች፣ የቀድሞ ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ በኮሌጁ የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አውደ-ርዕይ፣ የኪነ-ጥበብ ስራዎችና የባህል አልባሳት ትዕይንት ቀርበዋል።
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሚደቅሳ ከበደ በዚሁ ወቅት፤ የከተማ አስተዳደሩ የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ብቁ ሙያተኛ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሰልጣኞች በቂ ክህሎት እንዲጨብጡ ከኢንዱስትሪዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ከቴክኖሎጂ ዕውቀት ውጪ ልማትና ዕድገት ማረጋገጥ እንደማይታሰብ ጠቁመው፤ በዚህ በኩል ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በዓሉን ከማክበር ባለፈ በቴክኒክና ሙያ መስክ የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

Read More »
News

የሀገራችን ዕድገት ትልቁ ምሰሶ ሠራተኛው ነው ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ

የሀገራችን ዕድገት ትልቁ ምሰሶ ሠራተኛው ነው
ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
በኢትዮጵያ ለ51ኛ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ137ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) አስመልክቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዘንድሮው በዓል “የሠራተኛው መብት መከበር ለኢንዱስትሪ ሰላምና ለምርታማነት መሠረት ነው!” በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 23 ቀን በድምቀት የሚከበረውን የሜዴይ በዓል አስመልክቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን ለማስፈን በርካታ ሪፎርሞችን ማድረጉን ጠቁመው፣ አሰሪና ሠራተኛ ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አብራርተዋል።
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዜጎችን ደህንነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ጠቁመዋል።
መንግስት የሠራተኞችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው የሥራ ላይ ደህንነትን ለመጠበቅና አደጋዎችን ለመከላከል የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን(የኢሰማኮ) ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው የሠራተኛው መብት መከበር ለሀገር እድገትና ለምርታማነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚያደርገው አሰሪ፣ ሠራተኛና መንግስት በጋራና በትብብር የሚያከብሩት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሞገስ ቀኑን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የሠራተኛውን መብት የማያከብር አሰሪ ምረታማነቱን ከማሳደግ ይልቅ ጊዜውን በንትርክ ይጨርሳል ብለዋል፡፡
ይህንን ተገንዝበው በአሁኑ ወቅት በርካታ አሰሪዎች ለሠራተኞቻቸው ቅድሚያ በመስጠት አበረታች ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።
ከወዲሁ እንኳን ለአለም የሰራተኞች ቀን አደረሳችሁ!

Read More »
News

ቢሮው የISO 9001:2015 ትግበራን በይፋ ጀመረ

ቢሮው የISO 9001:2015 ትግበራን በይፋ ጀመረ
የአማራ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጡን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችለውን የቴክኒክ ድጋፍ ስምምነት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ስቡህ ገበያው እና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት በቀለ ፈርመዋል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ዶ/ር መሰረት በቀለ እንደገለጹት፣ የጥራት ማኔጅመንት ሥርዓትን መተግበር ተቋማት የተገልጋይ እርካታን በተጨባጭ እንዲያረጋግጡ ከመርዳቱም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።
ስምምነቱ ቢሮው ከክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ተያያዥ ጉዳዮች አኳያ የሚሰጠውን አገልግሎት ምቹ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችለው ተመላክቷል።
ቢሮው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በስሩ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ በጀመረው ጥረት፣ በ2017 በጀት ዓመት 5 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የISO ትግበራን አጠናቅቀው እውቅና ማግኘት ችለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ተጨማሪ 7 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን የጥራት ሥራ አመራር ስርዓት ማረጋገጫ ባለቤት ለማድረግ ዝግጅቶች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ መገባቱ ቢሮው አስታውቋል።

Read More »
News

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንተርፕራይዞችን . . .

በክልሉ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስገኝተዋል
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍና በማብቃት ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስገኘታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ “የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው አውደ ርዕይና ባዛር እንዲሁም የሞዴል ኢንተርፕራይዞች ደረጃ ሽግግር እውቅና መርሃ ግብር በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በክልሉ ኢንተርፕራይዞችን በማብቃት ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሸጋገር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት አስገኝተዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በክልሉ ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ስራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሙስጠፋ ኢሳ ናቸው።
በገጠርና በከተማ በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፍ ከ25 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ መስኮች መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ የሚገኙ 4ሺህ 948 ኢንተርፕራይዞችን የማሸጋገርና 495 ሞዴል ኢንተርፕራይዞችን የመለየት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል በሆሳዕና ከተማ የሚገኘው የጡማ ፕላስቲክ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ ሰለሞን ታሪኩ እና የእንጨትና የብረታብረት ማምረቻ ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ ወጣት ዘርፍነሽ ሽብሩ የደረጃ ሽግግሩ ድርጅቶቻቸው ስራቸውን በተጠናከረ ሁኔታ እንዲከውኑ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
ፋብሪካው ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገቡንና ከ150 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
ወጣት ዘርፍነሽ በበኩሏ ኢንተርፕራይዙ 10 ሚሊየን ብር ካፒታል ማስመዝገቡን ገልጻ 30 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል ብላለች። ዘገባው የኢዜአ ነው።

Read More »
News

ኢንተርፕራይዞች …

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የክልሉን ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ከፈቱ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በሆሳዕና ከተማ ለሚቀጥሉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ክፍት ሆኖ የሚቆየውን የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ከፍተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በአዲስ መልክ ለሁለተኛ ጊዜ በሚያካሄደው ኢግዚቢሽንና ባዛር የሞዴል ኢንተርፕራይዞች የደረጃ ሽግግርና ዕውቅና ፕሮግራም እንደሚኖር ቢሮው አስታውቋል ።
በባዛሩ በኢንዱስትሪና በግብርና የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን አጋጣሚው አምራቾችና ሸማቾች በቀጥታ የሚገናኙበት ሰፊ የገበያ ትስስር የሚፈጥር እንደሚሆንም የቢሮው ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ አስታውቀዋል፡፡
በዝግጅቱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፣የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ፣የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

Read More »
News

ፕሮጀክቱ በግብርና ዘርፍ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማላቅ የሴቶችና ወጣቶችን

ፕሮጀክቱ በግብርና ዘርፍ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማላቅ የሴቶችና ወጣቶችን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተገለጸ
የግብርና ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ለሥራ ፈጠራ (AMD4J) ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ የተገመገመ ሲሆን በተለይም የግብርና-ቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን ማጠናከር፣ የሥራ ማዕከላት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እና የፋይናስ አቅርቦትና ተደራሽነትን ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
በዚህም የወጣቶችንና የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ከመገንባት አኳያ ያለው ሚና የላቀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የግብርና ዘርፉንም ከማዘመን አኳያ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።
በተጨማሪም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሥራ ፈጣሪዎችን የመቋቋም አቅም ማሳደግ በሚቻልባቸው ስልቶች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
በዚህም የኢንተርፕራይዞችን አደጋ የመቋቋም አቅም ማጎልበት ፕሮጀክት፤ በተለያየ ምክንያት ችግር የሚገጥማቸውን ኢንተርፕራይዞች መልሶ ለማቋቋምና ችግሮችን የመቋቋም ዝግጁነታቸውን በማሻሻል የዜጎችን ኑሮ በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችል እንደሆነ የተመላከተ ሲሆን ስትሪንግ ኮሚቴው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡

Read More »
News

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም …

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ለሥራ ባህል ግንባታ መሠረት እየጣለ መሆኑ ተገለጸ
የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማትን የኩባንያዎች መፈልፈያ ለማድረግ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቀረፀውን አዲሱን የሪፎርም እሳቤ መነሻ በማድረግ፣ በርካታ ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም የሰልጣኞችን የሥራ ባህልና ክህሎት እያሳደጉ መሆኑ ተመላከተ።
የአማራ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገቢያው(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ሰልጣኞች ተግባራዊ ሥልጠናን በተጨባጭ ከማግኘታቸው ባለፈ፣ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲያዳብሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
ሰልጣኞች በተጨባጭ እያመረቱ የሚማሩ መሆኑ የጊዜ አጠቃቀምን፣ ሥራን በአግባቡ መፈፀምን፣ እንዲሁም ኃላፊነትና ተጠያቂነትን በተግባር እንዲለማመዱ ዕድል እየፈጠሩላቸው መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።
ዶ/ር ስቡህ አክለውም፣ ይህ አሠራር ሰልጣኞች በሥራ ቦታ የሚፈለገውን የዳበረ ሥነ-ምግባር እንዲያጎለብቱ ከመርዳቱም በላይ፣ በቡድን የመሥራት፣ የመግባባትና የመተባበር ክህሎታቸው እንዲያድግ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። እነዚህ እሴቶች ሰልጣኞች ወደፊት ወደ ሥራው ዓለም ሲሰማሩ በቀላሉ እንዲላመዱና ውጤታማ እንዲሆኑ አስተማማኝ መሠረት ይጥላሉ።
በኮሌጆች ውስጥ የሚቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች የሰልጣኞችን የኢንተርፕርነርሽፕ አስተሳሰብ (Entrepreneurial mindset) በማሳደግ ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ስቡህ፤ ሰልጣኞች የገቢና ወጪ ቁጥጥርን እንዲሁም የገበያ ትስስርን በተግባር እንዲያውቁ በማድረግ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ያላቸውን ተነሳሽነትና በራስ መተማመን እንደሚያሳድጉት ጠቁመዋል። ይህም ጥራትን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ላይ በማተኮር በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የመሆን አቅምን ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።
በአጠቃላይ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ሰልጣኞችን ከንድፈ-ሀሳብ ባለፈ ለተግባራዊ ዓለም የሚያዘጋጅ ስትራቴጂ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

Read More »
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
somSOM
Scroll to Top