Mols.gov.et

News

News

ከ26 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረው የከተማ ግብርና…

ከ26 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረው የከተማ ግብርና
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 8 ወራት ብቻ በከተማ ግብርና ዘርፍ ከ 26 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን እንደገለጹት፤ 2,088 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በቅጥር ከ 26 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ባለፉት 8 ወራት ከተፈጠረው 287 ሺህ በላይ ቋሚ የሥራ ዕድል ውስጥ የከተማ ግብርና የ 9.3 በመቶ ድርሻን ይዟል።
በከተማዋ የሥራ ዕድል ሊፈጠርባቸው የሚችሉ 44,307 የከተማ ግብርና ጸጋዎች ተለይተው ወደ ሥራ መገባቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ኢንተርፕራይዝ በማደራጀት ብቻ 17,404 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡
የከተማ ግብርና ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር የተሻገረ ፋይዳ እንዳለው የጠቆሙ ዳይሬክተሩ ለነዋሪዎች የዕለት ተዕለት የምግብ ፍጆታ የሚውሉ (አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ዶሮና እንቁላል…) የመሳሰሉ ምግቦች በራስ ግቢና አካባቢ በማምረት የኑሮ ውድነትን መቋቋም ያስችላል ብለዋል።

Read More »
News

የዘርፍን ውጤታማነት የማላቅ ግብ ያለው ቴክኒካዊ ድጋፍና ክትትል

የዘርፍን ውጤታማነት የማላቅ ግብ ያለው ቴክኒካዊ ድጋፍና ክትትል
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በዘርፉ የታቀዱ የለውጥ አጀንዳዎችና ስትራቴጂካዊ ግቦች ውጤታማ መሆናቸውን ለማረጋገጥ፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የሚከናወን መጠነ-ሰፊ የቴክኒክ ድጋፍና የመስክ ክትትል ሥራ ጀምሯል።
የክትትልና ድጋፍ ሥራውን የሚመሩት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ነቢሃ መሐመድ እንደገለጹት፤ ይህ የመስክ ምልከታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሀገራዊ ተልዕኮውን በስኬታማነት ለማስፈፀም የቀረፃቸውን እሳቤዎችን ተግባራዊነት ለመመዘን የሚያስችል ነው፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት በከፍተኛ አመራሮች የተመራ የክትትልና ድጋፍ ቡድን በ10 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ምልከታ ማድረጉን ያስታወሱት ክብርት ነቢሃ የታዩ ክፍተቶችን መሠረት በማድረግ ለክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና ለዘርፍ ቢሮ ኃላፊዎች በተሰጠው ግብረ-መልስ መሰረት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ዕቅዳቸውን ከልሰው ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡
ቴክኒካል ባለሙያዎችን ያካተተው የአሁኑ የመስክ ምልከታ ዋና ዓላማ በአመራር ደረጃ በቸካሄደው የድጋፍና ክትትል ሥራ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የገቡትን ቁርጠኝነትና የጀመሩትን የሥራ አፈጻጸም በተጠናከረ መልኩ እንዲፈጽሙ የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ይህ የሱፐርቪዥን ቡድን በየክልሎቹ ከሚገኙ አቻ የቴክኒክ ቡድኖች ጋር በቅንጅት በመሥራት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎት ልማትና በኢንዱስትሪ ሰላም ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን በቦታው በመገኘት የሚፈታና የልምድ ልውውጥ የሚያደርግ ይሆናል።
በመሆኑም በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ለክትትልና ድጋፍ ቡድኑ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ፣ የዘርፉን ሥራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ክብርት ነቢሃ ጥሪ አቅርበዋል።

Read More »
News

የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አዲስ ተስፋ…

የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አዲስ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣ የሚጠበቀው ስምምነት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ ያለውን አቅም ለማጠናከር እና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችለውን የጋራ የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል።
ይህ ስምምነት በትምህርት ላይ ብቻ ሳይወሰን በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ የበለጸጉ የቱሪስት መስህቦችን በተለይም የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የቱሪዝም ሀብቶች በዘላቂነት ለማልማትና ለማስተዋወቅ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በቴክኒክና በዕውቀት ለመደገፍ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።
የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ባለሙያዎች ለስምምነቱ መሳካት ላሳዩት ቁርጠኝነት የዩኒቨርሲቲው አመራር ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ አጋርነት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በዕውቀትና በክህሎት የሚመራ ብቁ የሰው ኃይል ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ስምምነት ተቋማቱ ያላቸውን አቅም በማቀናጀት ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አዲስ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣም ይጠበቃል።

Read More »
News

በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራ የሚያቆሙ ኢንተርፕራይዞችን …

በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራ የሚያቆሙ ኢንተርፕራይዞችን ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ሥራ የሚያቆሙ ወጣትና ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
ፕሮጀክቱ ኢንተርፕራይዞቹ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ዳግም ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲገቡ በማድረግ፣ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻልና የአካባቢዎችን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እንደሚያስችል ተመላክቷል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ዕድል ፈጠራ ማስፋፊያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘሪሁን ዓለማየሁ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በቅርቡ የጸደቀውን የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ በኢኮኖሚ ቀውስና በአደጋ ወቅት የኢንተርፕራይዞችን ተጎጂነት ለመቀነስ ፖሊሲው ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ወጣቶችንና ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ይህም ሚኒስቴሩ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ወደ ተጨባጭ የሥራ ዕድልና የኢኮኖሚ ድጋፍ ለመቀየር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ የሀገር ውስጥ ፕሮግራም ኦፊሰር ፓዋልም ኢልቡዶ በበኩላቸው፤ ባንኩ የአፍሪካን ወጣቶች የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ወደ ኢኮኖሚያዊ ኃይል ለመለወጥ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ይህ ፕሮጀክት ዘላቂ የሥራ ዕድልና ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።
የፕሮጀክቱን ዝርዝር አፈጻጸም በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አሺቅ በድሩ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ለአራት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ተመድቦለታል። ከዚህም ውስጥ 10 በመቶው በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ይሆናል።
ፕሮጀክቱ በዋናነት በአማራ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ ከ3,000 በላይ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ አቅርቦት፣ በክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠናን ጨምሮ በተለያዩ ድጋፎች ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

Read More »
News

ኢፍጣር፤ የአብሮነት መገለጫ!

ኢፍጣር፤ የአብሮነት መገለጫ!
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው የጋራ የኢፍጣር መርሃ ግብር በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቅጽርግቢ ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጨምሮ የባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ይህ የኢፍጣር መርሃ ግብር በረመዳን ወር የሚታዩትን የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ እና የመካፈል ታላላቅ መንፈሳዊ እሴቶች መሠረት ያደረገ ነው።
መሰል መርሃ ግብሮች በተቋሙ አመራርናሠራተኞች መካከል ያለውን አብሮነት በማጠናከር በመካከላቸው ያለውን ቤተሰባዊ ቅርርብን በማላቅ ለተቋማዊ ስኬትና ለሥራ ተነሳሽነት መሠረት የሚጥሉ ናቸው፡፡

Read More »
News

ምርትና ምርታማነትን ማጎልበት

ምርትና ምርታማነትን ማጎልበት፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ማመንጨትና ከባቢያዊ ችግሮችን መፍታት የሚጠበቅባቸው የቴክኒክና ሙያ ተቋማት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ከሥልጠና ማዕከልነት ባለፈ የኩባንያዎች መፈልፈያ፣ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያና የሥራ ዕድል ፈጣራ ማዕከላት እንዲሆኑ የሚያስችል አዲስ እሳቤን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
የዚህ እሳቤ ዋንኛ ዓላማ የስልጠና ተቋማቱ ያላቸውን ማሽኖችና ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ከባቢያዊ ችግርን የሚፈቱ ምርቶችን እንዲያመርቱ ፣ በሂደቱም በተግባር በተደገፈ መልኩ ሰልጣኞቻቸውን በክህሎት እንዲያበቁ ማስቻል ነው፡፡
በዚህ መሰረት በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ራሱን የቻለ ህጋዊ ኢንተርፕራይዝ አቋቁመው ወደ ሥራ እየገቡ ይገኛሉ፡፡
የመሰል ኢንተርፕራይዞች መቋቋም ተቋማቱ የውስጣዊ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ፣ ምርትና ምርታማነትን እንዲያጎለብቱና አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በማመንጨት የአካባቢቸውን ችግር እንዲፈቱ የሚያስችል አቅምን እንደሚያላብሳቸው ይጠበቃል፡፡

Read More »
News

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ሀገር በቀል ክህሎትን

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ሀገር በቀል ክህሎትን በማጎልበት የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው – የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዜጎችን የዲጂታል ፈጠራና ክህሎት ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው።
በተለይም በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሳይበር ደኅንነት ያሉ አዳዲስ የሥልጠና መርሃ ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
ለዚህም የክህሎት ማበልጸጊያ ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት የግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና መሰል ዘርፎችን ምርታማነት የሚያሻሽል ሀገር በቀል የፈጠራ ክህሎት እንዲጎለብት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት መሳለጥ መሰረት መጣሉንም ዋና ዳይሬክተሩ አውስተዋል።
የ2030ው ስትራቴጂ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ሥርዓቱን የበለጠ በማዘመን ረገድ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ሀገር በቀል የፈጠራ ክህሎትን በማጠናከር ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ምርምር ውጤቶችን እንዲያፈልቁ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም የሰልጣኞችን የቅበላ አቅም በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ወጣት ስራ ፈጣሪዎችም ስትራቴጂውና የተሰጣቸው ስልጠና ለስኬታቸው መነሻ መሆኑን ገልጸዋል። ።ዘገባው የኢዜአ ነው

Read More »
News

በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት

በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ የአሰራር ምኅዳር መፈጠሩ ተገለፀ
በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ የአሰራር ምኅዳር መፈጠሩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ።
ቢሮው በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከዛሬ መጋቢት 2/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የሥራ አውደ ርዕይ ከፍቷል።
“የግል ዘርፍ ተሳትፎ፤ የብቁ ወጣቶች ማንሰራራት ለገሀር ልዕልና” በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው የሥራ አውደ ርዕይ ላይ 6ሺህ የሚሆኑ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችና ሴቶች ቀጥተኛ ሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል እንደሚመቻች ተገልጿል።
የሥራ አውደ ርዕዩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መርቀው ከፍተውታል።
በዚሁ ጊዜ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት መሰረት እየጣለ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ሥራ ፈላጊዎችን በማደራጀት ከሥራ ቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍም ሥራ ፈላጊዎችና ቀጣሪዎችን የሚያገናኝ ምቹ ምህዳር መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ የ24/7 የሥራ ባህልም የከተማዋን ልማትና ዕድገት በማስቀጠል የበርካታ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የቢሮ ምክትልና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አስፋው ለገሰ በበኩላቸው፤ በሰባት ወራት ውስጥ ከ280ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሥራ አውደ ርዕዩ የሚሳተፉ ከ200 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚያስፈልጋቸውን የሰለጠነ የሰው ሃይል በመመልመል በርካታ ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ዘገባው የኢዜአ ነወ።

Read More »
News

በኦሮሚያ ክልል የእሴት ሰንሰለትን መሰረት በማድረግ …

በኦሮሚያ ክልል የእሴት ሰንሰለትን መሰረት በማድረግ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለዜጎች መፍጠር እንደተቻለ ተገለፀ
የኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና የክህሎት ቢሮ፣ የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና ህጋዊነት ዳይሬክተር አቶ ተማም ሁሴን እንደሚገልፁት በክልሉ በዶሮ እርባታ፣ በከብት ማድለብ፣ በንብ ማነብና በመሳሰሉት ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራዞችን በእሴት ሰንሰለት የማስተሳሰርና ውጤታማነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች እንቁላል አስፈልፍለው የአንድ ቀን ጫጩት የሚያስረክቡ፣ የእንቁላልና ሥጋ ዶሮዎችን የሚያረቡና ለገበያ የሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞችን በእሴት ሰንሰለት ለማስተሳሰር በተሠሩ ሥራዎች በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አቶ ተማም ይናገራሉ፡፡
የትስስሩን ውጤታማነት ለማረጋገጥም የብድር፣ የማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት የማመቻቸት ሥራ በሥፋት እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን በዶሮና በከብት መኖ ምርት ላይ ለሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሊዝ ፋይናንስን በመጠቀም ማሽኖች እየቀረበ እንደሚገኝም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ የእንስሳ መኖ ዝግጅት ጀምሮ በወተት ከብት እርባታና የወተት ተዋፅኦን አቀነባብረው ለገበያ የሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞችን ለማስተሳሰር እንዲቻልም የከብት እርባታ የክላስተር ማዕከላትን በሁሉም የኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች የማስፋት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በኢንተርፕራይዝ ተደደራጅተው በወል ቦታዎች ላይ የስንዴ እያመረቱ የሚገኙ ወጣቶችን ዱቄት፣ ዳቦና ኬክ ከሚያመርቱና ለገበያ ከሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞች ጋር የማስተሳሠር ሥራ ለመሥራት የሚስችል ዕቅድ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ጠቁመዋል ፡፡
ኢንተርፕራይዞችን በግብዓትና ምርት አቅርቦት በማስተሳሰር በርካታ የሰው ኃይልን ተሳታፊ የሚደርግ የሥራ ዕድል የመፍጠር ግብ ያለው ‹‹እሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ›› በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በተቀረፀው የዘርፉ አዲስ እሳቤ ውስጥ ከተካተቱ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

Read More »
News

“የኢንዱስትሪ ሰላም ለምርታማነት፣ ምርታማነት ለሀገራዊ ብልጽግና!”

“የኢንዱስትሪ ሰላም ለምርታማነት፣ ምርታማነት ለሀገራዊ ብልጽግና!”
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እና ለምርታማነትና ተግዳሮት የነበሩ ትርክቶችን ለመቀየር የሚያስችል አዲስ የሪፎርም እሳቤን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ግንኙነት ዴስክ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘለለው የሚኒስቴር መ/ቤቱ አዲስ የዘርፍ እሳቤ የኢንዱስትሪዎችንና የሠራተኞችን ተወዳዳሪነት የሚያልቅ ብሎም አቀፋዊ ዕድሎችንና ተግዳሮቶችን በአግባቡ የቃኘ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
በኢትዮጵያ ስለ ምርታማነት የሚነሱ ትርክቶች ብዙ ጊዜ በሁለት ተቃራኒ ጎራዎች እንደሚፈረጁ የሚገልጹት አቶ ውብሸት፤ በአንድ በኩል አሠሪዎች “ሠራተኛው ዝቅተኛ የሥራ ዲሲፕሊንና ክህሎት፣ የሥራ ባህል የሌለው፣ መብቱን ብቻ የሚጠይቅ፣ ግዴታውን የማይወጣና ምርታማነቱ ዝቅተኛ ነው” የሚል ትርክት እንደሚያራምዱ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ሠራተኞች “ሰብአዊ ክብራችን፣ ጤንነታችንና ደህንነታችን የማይጠበቅ እንዲሁም በሕግ የተቀመጠ መብታችንን እንዳንጠቀም ክልከላ ይደረግብናል፤ ለምርትና ምርታማነት የሚያጎለብቱ ሐሳቦች ቢኖሩንም የሚሰማን ባለመኖሩ ምርታማነታችን ቀንሷል” በሚል አሠሪዎችን ሲከስሱ ይደመጣል፡፡
መሰል አመለካከቶች ሥር መስደዳቸውና “የበዝባዥና ተበዝባዥ” ትርክት መጎልበቱ በኢንዱስትሪዎች ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጥሩና በኢንዱስትሪ ሰላም ላይ ጥላ ሲጥሉ ቆይተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያመላክቱት ምርታማነትን ከሰው ክብርና ጥቅም ነጥሎ ማየት እንደማይቻልም የሚሉት አቶ ውብሸት ሚኒስቴሩ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን በምርትና ምርታማነት ላይ ምክክር በማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን መፍታት የሚችል እና የኢኮኖሚ ሽግግርን የሚያረጋግጥ አዲስ የኢንዱስትሪ ባህል ለመገንባት ላለፉት ዓመታት “የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ ምክክር ለምርታማነት” ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዳሉ፡፡
ይህንንም ተከትሎ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በማደራደርና በማስማማት ፈጣን መፍትሔ የሚያገኙበት አሠራር በመዘርጋቱ የሥራ ማቆም አድማዎችንና የሥራ መስተጓጎሎችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል።
በሌላ በኩል ሠራተኛው ስለ መብቱና ግዴታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች የሥራ ተነሳሽነትንና ዲሲፕሊንን በማጎልበት የኢንዱስትሪዎችን የምርት ጥራትና ብዛት ማሳደግ ተችሏል።
ኢንዱስትሪ ማኅበረሰቡ (አሠሪ፣ ሠራተኛና መንግሥት) በጋራ በሚያደርጉት ምክክር፣ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ስልታዊ አቅጣጫዎች እየተቀመጡ ይገኛሉ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር “የኢንዱስትሪ ሰላም ለምርታማነት” የሚለውን መሪ ሃሳብ ለማሳካት፣ የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ምክክር ቀጣይነት ባለው መልኩ እስከ ታችኛው የዘርፉ መዋቅር እንዲሰርጽ በትኩረት እየሠራ መሆኑ የኢንዱስትሪው ማኅበረሰቡ ለምርታማነትና ለሀገራዊ ብልጽግና በጋራ የሚቆምበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አቶ ውብሸት ዘለለው ገልጸዋል።

Read More »
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
somSOM
Scroll to Top