Mols.gov.et

News

News

‹‹የጥራት ዓመት ››ግብን ለማሳካት በኢኒስቲትዩቱ የተካሄዱ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች

‹‹የጥራት ዓመት ››ግብን ለማሳካት በኢኒስቲትዩቱ የተካሄዱ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በጥናት፣ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ረገድ የያዘውን ‹‹የጥራት ዓመት ››ግብ ለማሳካት በታቀደው መሠረት በርካታ ሥራዎች ማከናወኑ ተገለፀ፡፡
የኢኒስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ(ዶ/ር) እንደሚገለጹት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 12 ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች ተጠናቀው ለተጠቃሚ እንዲበቁ ተደርገዋል።
በተጨማሪም ስድስት ጥናቶች በሂደት ላይ እንደሚገኙና ለ24 ተከታታይ ሳምንታት በተካሄደ የምርምር ሴሚናር 61 የጥናት ሥራዎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ጠቁመዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የባህል ማዕከል ማቋቋሙና በስነ-ጥበብ ሥራዎች የተቋሙን ገጽታ የመገንባት ሥራ ማከናወኑ እንዲሁም የምሩቃንን የቅጥር ሁኔታና የገበያ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ዘጠኝ የእሴት ሰንሰለት ጥናቶች መጠናቀቃቸውም ተመላክቷል።
የማህበረሰብ አገልግሎትን በተመለከተም ኢንስቲትዩቱ የሙያ ብቃቱን ወደ ህብረተሰቡ በማውረድ ረገድ ተጨባጭ ሥራዎችን አከናውኗል። “አንድ ተጨማሪ ክህሎት ለዜጎች” በሚለው መርሃ-ግብር 368 ሰዎች የሰለጠኑ ሲሆን በሌሎች 11 ተቋማት ደግሞ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች የልል ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።
ከዚህም ባሻገር ተንቀሳቃሽ የንግድ ኪዮስኮችን በመሰራት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ለማዕድ ማጋራት እና ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና አካል ጉዳተኞች የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን ሀብታሙ ሙሉጌታ(ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
መረጃው የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ነው፡፡

Read More »
News

ሚኒስቴሩ ከኦሮሚያ ባንክ ጋር…

ሚኒስቴሩ ከኦሮሚያ ባንክ ጋር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራረመ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ባንክ ጋር በመተባበር በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎት ልማትና በፋይናንስ አቅርቦት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ 70 በመቶው ወጣት ያለባት ሀገር እንደመሆኗ፣ ይህን የሰው ኃይል ወደ ስራ ለማሰማራት የፋይናነስ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው።
ኦሮሚያ ባንክ ራሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያደራጀ መሆኑ ከሚኒስቴሩ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (LMIS) ጋር ተዳምሮ ወጣቶች በቀላሉ የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ባንኮች ስለ ስልጠና ሳይጨነቁ ሚኒስቴሩ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮቹ ያሰለጠናቸው “እጃቸው ለሥራ የተፍታታ” ዜጎችን ያቀርባል ያሉት ክብርት ሚኒስትር ይህንን መነሻ በማድረግ የኦሮሚያ ባንክ የዲጂታል ብድር አሰራር ከሚኒስቴሩ ቴክኖሎጂዎችና መዋቅሮች ጋር ተሳስሮ ከቅድመ ብድር እስከ ማስመለስ ያለውን ሂደት በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
የርቀት ሥራ ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር የሥራ ዕድሎችን በጋራ ከመስራ ባሻገር ለየት ያለ ክህሎት ያላቸው የወጣቶችን ተሰጥኦ በመመንዘር ወደ ሀብት መቀየር የሚያስችሉ ስራዎች በትብብር እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ተፈሪ መኮነን በበኩላቸው፣ ሚኒስቴሩ በቴክኖሎጂ የታገዘና ከዘመኑ ቀድሞ የሚራመድ ሥራ እየሰራ መሆኑን አድንቀዋል።
ባንካቸው ማህበረሰብ ተኮር በመሆኑ፣ ይህ ስምምነት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ለመቀየር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ከሚናገረው በላይ በተግባር እጅግ አስደናቂ ሥራዎችን እየከወነ መሆኑን በአካል ተመልክተናል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው እኛም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የብድር ሥርዓታችንን በመጠቀም፣ ወደ ውጭ ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎችን ጨምሮ የሁሉንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

Read More »
News

የቴክኖሎጂ ባለቤቶች በገበያ ላይ ያላቸውን

የቴክኖሎጂ ባለቤቶች በገበያ ላይ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ የሆነ ስምምነት
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመ።
የስምምነቱ ዋና ዓላማ በ”ክህሎት ኢትዮጵያ” ፕሮግራም የሚፈልቁ የፈጠራ ስራዎች ህጋዊ የአእምሯዊ ንብረት እውቅና እና ጥበቃ እንዲያገኙ ማስቻል ነው።
ከፊርማው ቀደም ብሎ የባለስልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች በኢንስቲትዩቱ የሚገኙ የፈጠራ ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን እነዚህን ውጤቶች እንዴት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚቻልም መክረዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር የክህሎት ኢትዮጵያ የፈጠራ ፕሮግራም ሀገሪቱን በተለያዩ ዘርፎች ሊለውጡ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች የሚፈልቁበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የፈጠራ ባለቤትነት እውቅና ማግኘት ፈጣሪዎች ለስራዎቻቸው ህጋዊ ጥበቃ እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክቶቻቸውን ለማሳደግ ከሚያግዙ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር እና በገበያ ላይ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አያይዘውም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ችግር ፈቺ ስራዎች እውን እንዲሆኑ ተቋማት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው በማሳሰብ ላለፉት ሁለት ዙሮች የተከናወኑ ተግባራትንና ለሦስተኛው ምዕራፍ የታቀዱ ዝግጅቶችን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እራሷን እንድትችልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ለፈጠራ ስራዎች እውቅና መስጠት ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በዚህ ዘርፍ ላይ በስፋት ባለመሰራቱ ምክንያት የፈጠራ ባለሙያዎች ተስፋ የመቁረጥና የመገታት እንቅፋት ሲገጥማቸው መቆየቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ባለስልጣኑ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀዳለ ተክሉ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው ትብብር ከመጀመሪያው ጀምሮ የጠነከረ መሆኑን ገልጸዋል። የፈጠራ ስራዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው ምክንያት እስካሁን ይገጥሙ የነበሩ በርካታ ችግሮች በዚህ አዲስ ስምምነት አማካኝነት መፍትሄ እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

Read More »
News

የሥራ ባህል ግንባታ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት

የሥራ ባህል ግንባታ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን የኩባንያዎች መፈልፈያ ለማድረግ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተቀረፀውን አዲሱን የሪፎርም እሳቤ መነሻ በማድረግ በርካታ የሥልጠና ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን እያቋቋሙ ይገኛሉ፡፡
ኢንተርፕራይዞቹ ሰልጣኞች ተግባራዊ ሥልጠናን በተጨባጭ የሚያገኙባቸው እንደመሆናቸው ጠንካራ የሥራ ባህል ከማዳበር አንፃርም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የሥራ ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ሸዋቀና ወልደ አማኑኤል እንደሚያብራሩት ኢንተርፕራይዞች ውስጥ የሚሳተፉ ሰልጣኞች የጊዜ አጠቃቀምን፣ ሥራን በአግባቡ መፈፀምን፣ እንዲሁም ኃላፊነትና ተጠያቂነትን በተግባር ይለማመዳሉ።
ይህም በሥራ ቦታ የሚፈለገውን የዳበረ ሥነ-ምግባር እንዲያጎለብቱ ከመርዳቱም በላይ በቡድን የመስራት፣ የመግባባትና የመተባበር ክህሎታቸው እንዲያድግ ያደርጋል። እነዚህ እሴቶች ሰልጣኞች ወደፊት ወደ ሥራው ዓለም ሲሰማሩ በቀላሉ እንዲላመዱና ውጤታማ እንዲሆኑ መሰረት ይጥላሉ።
በተጨማሪም በተቋማቱ ውስጥ የሚቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች የሰልጣኞችን የኢንተርፕርነርሽፕ አስተሳሰብ (Entrepreneurial mindset) በማሳደግ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አቶ ሸዋቀና ገልጸዋል።
ሰልጣኞች የገቢና ወጪ ቁጥጥርን እንዲሁም የገበያ ትስስርን በተግባር እንዲያውቁ በማድረግ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ያላቸውን ተነሳሽነትና በራስ መተማመን ይጨምራል። ይህም ጥራትን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ላይ በማተኮር በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የመሆን አቅምን ይፈጥርላቸዋል።
ባጠቃላይ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ሰልጣኞችን ከንድፈ-ሀሳብ ባለፈ ለተግባራዊ ዓለም የሚያዘጋጅ ስትራቴጂ ነው።
ይህ አሰራር ሰልጣኞች በሙያዊ ክህሎት የበለፀጉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውና የሥራ ዲሲፕሊን የተላበሱ እንዲሆኑ በማድረግ ወደ ሥራ ገበያው ሲገቡ የተሻለ ተመራጭነት እንዲኖራቸው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው መሪ ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል፡፡

Read More »
News

የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓቱ ስራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር

የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓቱ ስራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ስራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የዲጂታል ሥርዓቱን ተደራሽነት ከማስፋቱም በላይ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ አማካይነት አዳዲስ የሥራ አማራጮች እንዲፈጠሩ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ሥርዓት የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የተዘጋጀ ዲጂታል መድረክ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር እና በየዘርፉ ያሉ ክፍት የሥራ መደቦችን በአንድ ማዕከል የማሰባሰብና የሰው ኃይሉን በዘመናዊ መረጃና ክህሎት በመገንባት ለዓለም አቀፍ ገበያ ጭምር ብቁ ማድረግ ከገበያ መረጃ ስርዓቱ ዓላማዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ስራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ስርዓቱ ተግባራዊ ከተደረገ ከአራት ዓመታት በላይ እንደሆነው አንስተው፤ በዚህም ለአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ዜጎች በውጭ ሀገራት ስራ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡።
በሀገር አቀፍ ደረጃም 45 ሺህ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ስራ ፈላጊ ወጣቶች ስራ ቅጥር እንዲፈጽሙ ስርዓቱ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የዲጂታል ሥርዓቱን ተደራሽነት ከማስፋቱም በላይ በፋይናንሻል ቴክኖሎጂ አማካይነት አዳዲስ የሥራ አማራጮች እንዲፈጠሩ ረድቷል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የዲጂታል ፕላትፎርምን በመጠቀም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አንስተው፤ ይህንንም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓቱ በውጭ ሀገራት የርቀትና የፍሪላንስ የስራ አማራጮች እንዲሁም በአገር ውስጥ በቴክኖሎጂ የታገዙ የስራ አማራጮች ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ቁጥር እንዲያድግ እያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው።

Read More »
News

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት እና የብራዚል..

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት እና የብራዚል-ኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት ስትራቴጂያዊ አጋርነት መሰረቱ
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የኢንዱስትሪ ክህሎት ክፍተቶችን በዓለም አቀፍ ትብብር ለመሙላት ከብራዚል ከፍተኛ ተወካዮች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታወቀ።
ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለተሟላ አጋርነትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ተመላክቷል።
የብራዚል የክብር ቆንስላ ክቡር ልዊዝ ፈርናንዶ ዳ ሮቻ እና የብራዚል-ኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሮናልዶ ፔሬራ ባሬቶን ያካተተው ልዑካን ቡድን፤የኢንስቲትዩቱን የሥራ ማዕቀፍ፣ ስኬቶችንና በቀጣይ የጋራ ትኩረት በሚሹ ዘርፎች ላይ ከኢኒስቲትዩቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቢሩክ የልዑካን ቡድኑ ላሳየው ንቁ ተሳትፎ ምስጋናቸውን ገልጸው፣ የቀረቡትን የትብብር መስኮች በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ሮናልዶ ባሬቶ በበኩላቸው፣ በብራዚልና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የቆየ ትብብር መሠረት በማድረግ፣ በሥልጠና የታገዘ የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማምጣት ዘላቂ የሰው ኃይል ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚፈረመው የመግባቢያ ሰነድ (MoU) የሚከተሉትን ስልታዊ የትብብር መስኮች ያካተተ ይሆናል፦
ስምምነቱ በዋነኛነት ለኢትዮጵያ አሰልጣኞች የ”አሰልጣኞች ሥልጠና” ለማስጠት፣ ሁለትዮሽ ቴክኒካል የልምድ ልውውጦችን፣ አጭር ጊዜ የኢንዱስትሪ ሥልጠናዎችና የፒኤችዲ (PhD) ፕሮግራሞች፣ የጋራ ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትን የሚመለከቱ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
በዚህ አጋርነት ስድስት ቅድሚያ የሚሰጣቸው የሥልጠና ዘርፎች የተለዩ ሲሆን፤ እነሱም ሜካኒካል ጥገና፣ የኢንዱስትሪ መሣሪያዎችና ማሽነሪዎች፣ የነዳጅና ጋዝ፣ ማዕድንና ማቀነባበር፣ ኤሌክትሪካልና ኦቶሜሽን ሲስተም እንዲሁም ብየዳና ፋብሪኬሽን ናቸው።

Read More »
News

ስምንት መቶ ሺህ የገጠር ወጣቶች ተጠቃሚ…

ስምንት መቶ ሺህ የገጠር ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርገው ራዕይ 2 (RAYEE II) ፕሮግራም ወደ ትግበራ ሊገባ ነው
በኢትዮጵያ በገጠር ለሚገኙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግባራዊ የሚደረገው ራዕይ 2 (RAYEE II) ፕሮገራም የከፍተኛ አመራር የስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት ተካሄዷል፡፡
መንግስት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽንና ከኤስ ኤን ቪ(SNV) ጋር በመተባበር የሚተገብረው ይህ ፕሮግራም፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ 800 ሺህ ለሚሆኑ የገጠር ወጣቶች ጥራት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ነው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታና የፕሮግራም አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በመክፈቻ ንግግራቸው ፣ ራዕይ 2 (RAYEE II) ፕሮግራም 90 በመቶ ተጠቃሚዎች ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው ከመደበኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ስር የሰደዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍና ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ የተነደፈ ነው ብለዋል።
አክለውም ፕሮግራሙ ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ከሀገራዊ የልማት ግቦች ጋር ተሳስሮ ይፈጸማል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም የሀገርን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ተግባራዊ እየተደረገ ከሚገኘው የሌማት ቱሩፋት ( በዶሮ እርባታ፣ በወተትና በአትክልትና ፍራፍሬ) ዘርፎች ጋር በማስተሳሰር ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ የሚመሩት ይህ ፕሮግራም፣ በሰባት የሀገሪቱ ክልሎች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።
በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመውና በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚመራው ይህ ስትሪንግ ኮሚቴም በቀጣይነተ በአተገባበር ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየገመገመና እየፈታ ይሄዳል ተብሏል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ (Phase I) ከ278 ሺህ በላይ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር የቻለው ራዕይ (RAYEE)፣ አሁን በሁለተኛው ምዕራፍ በላቀ በጀትና ስትራቴጂ የኢትዮጵያን የገጠር ኢኮኖሚ ማነቃቃት እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

Read More »
News

የኢንተርፕራይዞች ምርታማነት ለሀገር ብልጽግና…

“የኢንተርፕራይዞች ምርታማነት ለሀገር ብልጽግና”፦ ታላቁ አውደ ርዕይ በመስቀል አደባባይ በደመቀ ሁኔታ ተከፈተ!
የመዲናችን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆኑት ኢንተርፕራይዞች የሥራ ውጤታቸውን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል! በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ አዘጋጅነት የሚካሄደውና ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆየው ዓመታዊ የኢንተርፕራይዞች ሳምንት አውደ ርዕይና ባዛር በመስቀል አደባባይ በደመቀ ሁኔታ ተከፍቷል።
የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በመክፈቻው ላይ እንደገለጹት፣ መንግስት የሰው ኃይልን ወደ ምርታማነት ለመቀየር ባደረገው ጥረት ባለፉት ዓመታት ብቻ ከ2 ሚሊዮን በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ዘርፉ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና ለኢንዱስትሪ ሽግግር ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል። ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ብቻ ለ11,605 ኢንተርፕራይዞች ከ13.5 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩንም አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ለ5,983 አንቀሳቃሾች 2.8 ቢሊዮን ብር ብድር የቀረበ ሲሆን፣ ለ1,571 ኢንተርፕራይዞች የ706.3 ሚሊዮን ብር የመሣሪያ ሊዝ ድጋፍ ተደርጓል። 10,921 ኢንተርፕራይዞች ደግሞ ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ ደረጃ መሸጋገራቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡

Read More »
News

ከአሰልቺ አሠራር ወደ ቀልጣፋው የአገልግሎት ማዕከል(መሶብ)

ከአሰልቺ አሠራር ወደ ቀልጣፋው የአገልግሎት ማዕከል(መሶብ)
የሥራ ባህል ለውጥ በሀገራችን ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ጀምሮ በመጨረስ እና የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በማዘመን ሂደት እየተገለጠ ይገኛል፡፡
ከልማት ፕሮጀክቶች አኳያ በኮሪደር ልማትና በሌሎችም ግንባታዎች ላይ የምናየው የቀንና ሌሊት ትጋት፣ ሥራን የዜግነት ክብር አድርጎ የማየት ባህል እየዳበረ መምጣቱን ያሳያል። በተመሳሳይ መንግስት ዜጎችን ከእንግልት ለማዳን በመሶብ አንድ ማዕከል ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለዜጎች በማቅረብ ረገድ አርአያ የሚሆን ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎታቸውን እያቀረቡ ከሚገኙ ተቋማት መካከል ደግሞ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ እድሳት እና ክሊራንስ የመሳሰሉ አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የሥራና ክህሎት ቢሮ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ አስገብተው ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽ ከተደረገባቸው ክልሎች አንዱ የሆነው የሲዳማ ክልል በማዕከሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች የኢንተርፕራይዝ ምዝገባ እና የሥራ ምዝገባ ይገኙበታል፡፡ በዚህም ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆኑ የሲዳማ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከፍያለው ከበደ ገልጸዋል፡፡
የሥራ ባህል ምንነት በዋናነት የሚለካው ለተገልጋይ በሚሰጥ ክብርና ለጊዜ በሚሰጥ ዋጋ ነው ያሚሉት አቶ ከፍ ያለው ቀደም ሲል አንድ ዜጋ የሥራ ምዝገባ፣ ንግድ ለመጀመር ወይም ልዩ ልዩ ፈቃዶችን ለማግኘት በየመሥሪያ ቤቱ ሲንከራተትና ሲንገላታ ይስተዋል ነበር። አሁን ግን የመሶብ አንድ ማዕከል ይህንን እንግልት በማስቀረት ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ጣራ ስር እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
እንደ አቶ ከፍያለው ገለጻ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥን ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት በማድረግ አዲስ የሥራ ባህል መፍጠር አስችሏል።
አገልግሎቱ ተደራሽ በሆነባቸው አካባቢዎች እንደ ኮሪደር ልማቱ ሁሉ፣ በመሶብ ማዕከላትም የሚታየው ቁርጠኝነት አገልግሎቶች በተቀመጠላቸው የሰዓት ገደብ (Service Level Agreement) እንዲጠናቀቁ ከማድረጉም በላይ የመንግሥት ሠራተኛው ለዜጎች ያለውን አገልጋይነትና ለሥራው ያለውን ታማኝነት በተግባር የሚያሳይበት መድረክ ሆኗል።
አንድ ፕሮጀክት በወቅቱ ሲጠናቀቅ ሀገር እንደምታተርፈው ሁሉ፣ አንድ ዜጋ አገልግሎትን ያለ እንግልት ሲያገኝም ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንግልት ሲቀንስ ዜጋው ጊዜውንና ጉልበቱን ምርታማነት ላይ ያውላል።
መሶብ አንድ ማዕከል ይህንን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ ዜጎች በሀገራቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑና በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረጉን ቀጥሏል።

Read More »
News

“የሥራ ፈጠራ ሥነ-ምህዳሩን በማጠናከር ረገድ …

“የሥራ ፈጠራ ሥነ-ምህዳሩን በማጠናከር ረገድ ስኬታማ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው”፤
የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት
በሀገራችን የሥራ ፈጠራ ሥነ-ምህዳሩን (Entrepreneurship Ecosystem) በማጠናከርና ወጣቶች ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የንግድ ሐሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ስልታዊ ድጋፎችን እያከናወነ ይገኛል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀሰን ሁሴን እንደገለጹት፤ ተቋማወጣቶች የራሳቸውን የፈጠራ ሐሳብ ይዘው ሲመጡ፣ ያ ሐሳብ ወደ ውጤታማ ኢንተርፕራይዝ እንዲያድግ የሚያስችል የክህሎት፣ የማማከርና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት ላይ ነው።
ዶክተር ሀሰን አክለውም፣ ከክህሎት ድጋፍ በተጨማሪ የገበያና የፋይናንስ ትስስር ለሥራ ፈጣሪዎች ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም መሠረት ከባንኮችና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር ለፈጣሪዎች የብድርና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የማመቻቸት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ በገበያ ውስጥ የሚታዩ ስኬታማ ስታርታፖች የኢንስቲትዩቱ ስልታዊ ድጋፍ ውጤቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ አቅም በመጠቀም ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ የኢንተርፕረነርሽፕ ንቅናቄ በሀገራችን ያለውን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማፋጠን እንደ ትልቅ መፍትሔ የሚወሰድ መሆኑ በመድረኩ ተመላክቷል።

Read More »
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
tigTIG
Scroll to Top