Mols.gov.et

News

News

ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ…

ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የማስተባበርና የመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት አደረጃጀት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሴት ሠራተኞች ፎረም አባላት በፎረሙ መተዳደሪያ ደንብ እና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያዩ፡፡
በዋናነት ሴቶች እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ፣ አቅማቸውን እንዲገነቡ እና በሥርዓተ ፆታ እኩልነት ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱን መቋቋም ተከትሎ ፎረሙ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ እምዬ ቢተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ፎረም የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሠራ መሆኑን ገልፀው በሥራ ቦታ ላይ የሴቶች መብትና ክብር በአግባቡ ተጠብቆ መሰራቱን በቅርበት የሚከታተል ቁልፍ አደረጃጀት ነው ብለዋል፡፡
ሴቶች መብታቸውን አስከብረው ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የማስተባበርና የመከታተል ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር በሚገኙ ሦስቱም ዘርፎች ማለትም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎት ልማትና በሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ውስጥ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፎረሙ መመሥረት ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የሴቶችን አቅም ማሳደግ፣ የሚደርሱ ጥቃቶችንና በደሎችን በጋራ መከላከል እንዲሁም ልምድና ተሞክሮዎችን መለዋወጥ የፎረሙ ዝርዝር ዓላማዎች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡
አደረጃጀቱን ይበልጥ የማጠናከር ሥራ ከሁሉም አባላት እንደሚጠበቅ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን ተሳታፊዎቹ በቀረቡት የመተዳደሪያ ደንብና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በጥልቀት መክረውና በሙሉ ድምጽ አፅድቀው ውይይቱን አጠናቀዋል፡፡

Read More »
News

መንግሥት ለጀመረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ኢንተርፕራይዞች .

‹‹መንግሥት ለጀመረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንትና ዋና ሞተሮች ናቸው ››
ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ፣ የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ፣ ሚኒስትር ዴኤታ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለዘርፉ አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፖሊሲ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡
የስልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰሎሞን ሶካ፤ መንግሥት ለጀመረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንትና ዋና ሞተሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞች ይህን ወሳኝ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የተቀረፀው የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፖሊሲ የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመቅረፍ ፣ ዕድገትን ለማስቀጠልና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቁልፍ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዘርፉ የነበሩ ድጋፎች የተበጣጠሱና አካታች ባለመሆናቸው ኢንተርፕራይዞች በአንድ ደረጃ ላይ ተንጠልጥለው እንዲቀሩ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ አዲሱ ፖሊሲ እነዚህን ማነቆዎች በዘላቂነት ለመፍታት የተዘጋጀ ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንተርፕራይዞች በሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ላይ ዋንኛ ተዋናይ ወደሚሆኑበት ደረጃ እንዲሻገሩ የተፈጠረውን ምቹ የፖሊሲ አውድ በመጠቀም ለተግባራዊነቱ እያንዳንዱ የዘርፉ አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ርብርብ እንዲያደርጉ ክቡር አቶ ሰለሞን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ የሚተገበረው ‹‹ በግብርና ኢንተርፕራይዞች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክት የፖሊሲውን ሰነድ በማሳተም፣ በማሰራጨትና የግንዛቤ መስጨበጫ መድረኩን በማዘጋጀት ላበረከተው የላቀ አስተዋጽዖም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

Read More »
News

በጋራ እንፈጥራለን

በጋራ እንፈጥራለን
የሥራና ክህሎት ሚንስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የሚያዘጋጀው የቴክኖሎጂ ባህል ግንባታ ፓነል ውይይት ለአምስተኛ ዙር «በጋራ እንፈጥራለን» በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጸዳለ ተክሉ እንደገለጹት፤ ይህ የፓናል ውይይት በቡድን ስራ ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ምክረ-ሀሳብ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
ስለ ኢኖቬሽንና ፈጠራ ሲነሳ የቡድን ስራ ወሳኝ ተግባር መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ኢንስቲትዩቱ ለፈጠራ ባለሙያዎች አርአያ እንዲሆን የተለያዩ ዘርፎች እርስበርስ መተሳሰር እንዳለባቸውና በዘርፉ ያሉ በርካታ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ለማሳካት የቡድን ስራ የግድ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በጋራ መስራት እውቀትን፣ ክህሎትን እና ችሎታን በማቀናጀት የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ግኝቶችን ለመፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል።
በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ላይ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑት ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የዕለቱ የፓናል ውይይት ዋና ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን በጋራ መስራታቸው ለፈጠራ ስራቸው ያበረከተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለታዳሚ ወጣቶች ልምዳቸውን አካፍለዋል።
ወጣቶቹ ሀመረ፣ ሩት፣ ያብስራ እና ሪሃና “የተንቀሳቃሽ የአእምሮ ግፊት መከላከያ መሳሪያ” ላይ ያመጡትን አዲስ የፈጠራ ስራ በሂደቱ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች እና በጋራ ያሳለፉትን ጠንካራ ተሞክሮ አቅርበዋል።
እነዚህ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ወደፊትም ፕሮጀክታቸውን ይበልጥ በማሳደግ ወደ ምርት ለማሸጋገር እና ለሀገራችን የጤና ዘርፍ ትልቅ መፍትሄ ለማምጣት በርትተው እንደሚሰሩ በቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በኢንስቲትዩቱ የሊደርሽፕና ማኔጅመንት ፋኩልቲ አማካኝነት በቡድን ስራ ውጤታማነት፣ ተግዳሮቶች እና ሊከተሏቸው በሚገቡ ስልታዊ አካሄዶች ላይ ያተኮረ መወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በቡድን መስራት በዘላቂነት ትርፋማ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን ከታዳሚዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በአጠቃላይ በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ባህልን ለማስረጽ የተጀመረው ይህ የፓነል ውይይት መድረክ በየጊዜው ሰፊና በጎ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች እየተገኙበት መሆኑ ተመላክቷል።
መረጃው የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢኒስቲትዩት ነው፡፡

Read More »
News

ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር..

ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በለውጡ መንግሥት የተተገበሩ የሪፎርም ሥራዎች የወጣቶችን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተጨባጭ ውጤቶችን አስገኝተዋል።
ባለፉት 4 ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ለ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠራቸውን ጠቁመው፣ ከዚህም መካከል 75 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለውጡ ካስገኛቸው ዋና ዋና ስኬቶች መካከል ወጣቶች ከተለመደው የቅጥር ሐሳብ ወጥተው ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩና ለሌሎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፈጠራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የቤተሰብ የንግድ ሥራዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አክለዋል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች መስፋፋትና ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ለወጣቶች ዘመናዊ፣ ፈጣንና ምቹ የሥራ ዕድሎችን የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ የዲጂታል የሥራ ገበያ ላይ የሀገሪቱንና የወጣቶቹን ተወዳዳሪነት ማሳደጉን አብራርተዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ በበኩላቸው፤ ከለውጡ በኋላ የወጣቶችን አቅም በማሳደግ ረገድ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ተስፋ ሰጪ፣ ዘላቂና ክህሎት መር የሥራ ዕድሎችን በተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ትልቅ አቅም መገንባቱን አብራርተዋል።
በመዲናዋ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት ጋሻው ዓለሙ የመኪና ጎማና ባትሪዎችን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ ላይ መሰማራቱን ጠቅሷል፡፡
የምናመርታቸው ምርቶች የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስና ቆሻሻን ወደ ሀብት ከመቀየር ባለፈ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን የሚያሳድጉና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብሏል።
በማኅበር በመደራጀት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ የቤትና የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችን እያመረቱ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ ወጣት አስቻለው ጌትዬ ነው፡፡
በቀጣይም የምርቶቻቸውን የገበያ ተደራሽነትና የሥራ ዕድሎችን ይበልጥ ለማስፋፋት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግሯል። መረጃው የኢዜአ ነው።

Read More »
News

በ270 ቀበሌዎች 32000 ወጣት ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል…

በ270 ቀበሌዎች 32000 ወጣት ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ስምምነት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በክህሎት ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ‹ ፖፑሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል› (PSI/E) ከተሰኘ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋማ ጋር ተፈራረመ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ( ዶ/ር ) በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያስፈፅማቸው ተልዕኮዎች የባለድርሻ አካላትን ርብርብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በዚሁ መሠረት‹‹ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከበርካታ ተቋማት ጋር የመግባባያ ሰነድ በመፈራረም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በአጋርነት እያከናወነ ይገኛል›› ብለዋል፡፡
ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ “ደረጃውን ወደጠበቀና ወደ ምሉዕ የሥራ እድል ማደግ” (Step Up to Dignified and Fulfilling Work) በሚል ስያሜ ለሦስት ዓመታት የሚተገበረው ይህ ፕሮግራም በአጠቃላይ 32 ሺህ ወጣት ሴቶችን ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህ ፕሮግራም ስር 32 ሺህ ለሚሆኑት ወጣት ሴቶች የፋይናንስ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ የሚሠራላቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 24 ሺህ ለሚሆኑት ወጣት ሴቶች ደግሞ የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ይሰራል፣ በተጨማሪም ከ4 ሺህ በላይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንደሚፈጠሩ በዕቅዱ ተካቷል፡፡
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በፌዴራል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በፖፑሌሽን ሰርቪሰስ ኢንተርናሽናል (PSI) መካከል በጋራ ዲዛይን በማድረግ (co-creation) የተጀመረ ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም ዕድሜያቸው ከ15-35 ለሆኑ ወጣት ሴቶች የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ፣ የትምህርት፣ የክህሎት እንዲሁም የሥራ ዕድሎችን በማስፋት የድህነት ቅነሳን ማፋጠን ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በተለይም የመሰረተ ልማት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ወጣቶችን የአካታች እድገትን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ የማህበረሰብን ችግሮች ለመፍታት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ይህ የረጅም ጊዜ አጋርነት የፕሮጀክቱ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ለታለሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድልን የማስገኘት ስትራቴጂካዊ ግብን እንደሚያሳካ ታምኖበታል፡፡

Read More »
News

የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ ፀደቀ

የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ ፀደቀ
የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) 114ኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በጄኔቫ ሲጠናቀቅ፣ በዲጂታል ዘመን የሥራ ገበያን የሚመራ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የፕላትፎርም ኢኮኖሚ የሥራ ደረጃ (Convention) በሰፊ ድምፅ በማፅደቅ ታሪካዊ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ይህ አዲስ ኮንቬንሽን በዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ የሚመሠረት ሥራ (platform work) ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች የሥራ መብት፣ የሥራ ደህንነት፣ የፍትሃዊ ክፍያ እና የማህበራዊ ጥበቃ መርሆዎችን ለማጠናከር ዓለም አቀፍ መሠረት ይጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ንቁ ተሳትፎ አድርጓል፡፡
ልዑካኑ በአሠሪዎችና በሠራተኞች ኮንፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ በመሆን በተለያዩ ኮሚቴዎች ውይይቶች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
በውይይቶቹ የተነሱት ዋና ጉዳዮች መካከል የዲጂታል እና ፕላትፎርም ኢኮኖሚ ሽግግር፣ የሴቶች እኩል ተሳትፎ እና ጥቅም ማረጋገጥ፣ እንዲሁም ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን በማጠናከር ምርታማነትን ማሳደግ ይገኙበታል፡፡
አዲሱ የተፀደቀው ዓለም አቀፍ የሥራ ደረጃ በተለይ በፈጣን የዲጂታል ዘመን ላይ የሚሰሩ ሠራተኞች በግልፅ የሥራ መብት እና የጥበቃ ስርዓት እንዲያገኙ የሚያስችል የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል በዲጂታል እና በአረንጓዴ የልማት ሽግግሮች ወቅት ሴቶች እኩል የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥርዓታዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በመንግስታት፣ በአሠሪዎች እና በሠራተኞች መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስታንዳርዶችን ማሻሻል ሌላው የተወያዩበት ዋና ነጥብ ነበር፡፡

Read More »
News

የሚሻሻለው የውጭ ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ…

የሚሻሻለው የውጭ ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ መመሪያ በሂደት የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን መተካት የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ አሰጣጥን ለማሻሻል ባዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል። ይህ አዲስ መመሪያ በሂደት የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን መተካት የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
በመድረኩ የተገኙት በሚኒስቴሩ የሥራ ስምሪት ማስፋፍያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ፈረዳ እንደገለጹት፤ መመሪያው የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የግል ዘርፉን የሚያበረታታ እና የሀገር ውስጥ ሠራተኞችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ተዘጋጅቷል።
አክለውም እስካሁን በሥራ ላይ የነበረው መመሪያ የቆየ በመሆኑ አሁን ላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከሚጠይቀው ፍላጎት አንጻር መመሪያውን ማሻሻልና ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ በበኩላቸው፣ መመሪያው አዲሱን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ሊሸፈኑ በማይችሉ ልዩ የሙያ መስኮች ላይ ብቻ የውጭ ዜጎችን በመቅጠር የሥራ ገበያውን ክፍተት ከመሙላት ባሻገር የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን በሂደት መተካት የሚችሉ ብቁ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት አላማው አድርጓል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የውጭ ዜጎች ያለአግባብ ወደ ሥራ ገበያው እንዳይገቡና የዜጎችን የሥራ ዕድል እንዳያጠቡ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እና ከታኅሣሥ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውን መመሪያ ከአዲሱ የአዋጅ ሥልጣን (አዋጅ ቁጥር 1156/2011) ጋር እንዲጣጣም እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

Read More »
News

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያዘጋጀው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ…

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያዘጋጀው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ‹‹አካታችነት››ን ዋንኛ ምሰሶ ለማድረግ የሚያግዝ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ አካሄደ
በመድረኩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የስትራቴጂክ ዕቅድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢብርሂም ሰይፉ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚያስፈፅማቸው የክህሎት ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ዘርፎች ሴቶችን፣ ወጣቶችን አካል ጉዳተኞችንና ሌሎችን ተጋላጭ የህበረተሰብ ክፍሎች ላይ በይበልጥ የሚያተኩሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚቀረፁ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና መመሪያዎች ከዚሁ አንፃር የተቃኙ ከመሆናቸውም በላይ አዲሱ የዘርፉ እሳቤ ውስጥም አካታችነት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ዜጎችን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሚኒስቴር መ/ቤቱ እያዘጋጀ በሚገኘው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ውስጥ አካታችነት ዋንኛ ምሰሶ እንዲሆን ለማስቻል መድረኩ በሴቶችና አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚዘጋጁ ዕቅዶችና አፈፃፀሞች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሚገባ እንዲያካትቱ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ከአካቶ ትግበራ አንፃር ሰፊ የአመለካለካከትና የተግባር ክፍተት የሚስተዋል በመሆኑ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት መሰራት እንደሚኖርባቸውም በተወያዮች ተመላክቷል፡፡
አካታችነት ላይ ያተኮሩ ትክክለኛ መረጃዎችን ማሰባሰብና በተለያየ አጋጣሚ የሚገኙ መረጃዎችንም ዜጎችን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም በአፅንኦት ተነስቷል፡፡

Read More »
News

በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ ላይ …

በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጀርመን የልማት ድርጅት(GIZ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ‹‹በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት መመሪያ ማሻሻያ እና በዲጂታል አሠራር ትግበራ›› ዙሪያ የሚያተኩር አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ከግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችና ጉዳዩ የሚመለከታው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳታፊ የሆኑበትን ይህን መድረክ በንግግር የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዜጎችን የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሪፎርም ሥራዎችን በቁርጠኝነት እያከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ዜጎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ተገቢውንና ክብር ያለው የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከነዚህ ስትራቴጂካዊ ሪፎርሞች መካከል ግንባር ቀደሙ የሥራ ገበያውን ዘመናዊና ተደራሽ ማድረግ ሲሆን፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (E-LMIS) የመበልጸግ ሥራ ተጠናቆ፣ ሥራና ሠራተኛ በዲጂታል ፕላትፎርም በቀላሉ የሚገናኙበት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል፡፡
መንግሥት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ለመወሰን መመሪያ ቁጥር 45/2013 አዘጋጅቶ ባለፉት አምስት ዓመታት ሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም አተገባበር ላይ በተደረጉ ዳሰሳ ጥናቶች የአፈጻጸም ክፍተቶችና ውስንነቶች መስተዋላቸውን ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችና የመብት ጥሰቶች መኖራቸውን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ጠቁመዋል፡፡
‹‹የመብት ጥሰት በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ ሲቀርብ፣ መንግሥት አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ያለማወላወል እንደሚወሰድ ሁሉም ወገን ሊገነዘበው ይገባል” ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የተሸሻለው መመሪያ ሠራተኛውን፣ አሠሪውንና ኤጀንሲዎችን በእኩልነትና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለተግባራዊነቱ ርብርብ እንዲያደርጉ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

Read More »
News

በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ከፍተኛ ውጤ

በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ
በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ የጥናትና ምርምር ጉባኤ እና የቴክኖሎጂ ውድድር፣ ኢትዮጵያውያኑ የፈጠራ ባለሙያዎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።
ከሰኔ 5 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ መድረክ ከ10 አገራት የቀረቡ 35 የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ 6ቱ ለፍጻሜ የደረሱ ሲሆን፣ 4ቱ ከኢትዮጵያ፣ 1 ከሕንድ እና 1 ከናይጄሪያ ነበሩ።
በመጨረሻው ውድድር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርናን ለማጎልበት የሚያስችል በIoT ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የመስኖ ክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ያቀረበው ዘላለም እንዳለው አንደኛ ደረጃን በመያዝ የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
አካልን ሳይጎዳ የጭንቅላት ውስጥ ግፊትን ለመለካት የሚያስችል CEREBRO-LOGIC የተሰኘ ፈጠራ ያቀረቡት ሩት ጌታቸው፣ ሀመረ፣ ያብስራ እና ሪሀና ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከናይጄሪያ የቀረበው የገቢ መረጃና ተከታታይነት ማረጋገጫ ሥርዓት (Revenue Intelligence and Traceability System) ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን በማግኘት የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ለአሸናፊዎቹ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት፣ ውጤቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች በምርምር፣ በክህሎትና በፈጠራ ያላቸውን አቅም በግልጽ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የፈጠራ ሥራዎቹ ከውድድር ባሻገር ወደ ሥራ እና ወደ ገበያ እንዲገቡ አስፈላጊ ድጋፎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በማጠቃለያው ሥነ ሥርዓት ላይ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን፣ ለአሸናፊዎችም እንደየደረጃቸው ሜዳሊያና ልዩ ሽልማቶች ተሰጥተዋል።

Read More »
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
tigTIG
Scroll to Top