Mols.gov.et

የሚሻሻለው የውጭ ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ…

June 17, 2026
የሚሻሻለው የውጭ ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ መመሪያ በሂደት የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን መተካት የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ስምሪት ፈቃድ አሰጣጥን ለማሻሻል ባዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል። ይህ አዲስ መመሪያ በሂደት የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን መተካት የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል። በመድረኩ የተገኙት በሚኒስቴሩ የሥራ ስምሪት ማስፋፍያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ፈረዳ እንደገለጹት፤ መመሪያው የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የግል ዘርፉን የሚያበረታታ እና የሀገር ውስጥ ሠራተኞችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ተዘጋጅቷል። አክለውም እስካሁን በሥራ ላይ የነበረው መመሪያ የቆየ በመሆኑ አሁን ላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከሚጠይቀው ፍላጎት አንጻር መመሪያውን ማሻሻልና ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ በበኩላቸው፣ መመሪያው አዲሱን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ሊሸፈኑ በማይችሉ ልዩ የሙያ መስኮች ላይ ብቻ የውጭ ዜጎችን በመቅጠር የሥራ ገበያውን ክፍተት ከመሙላት ባሻገር የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን በሂደት መተካት የሚችሉ ብቁ ኢትዮጵያውያንን ማፍራት አላማው አድርጓል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የውጭ ዜጎች ያለአግባብ ወደ ሥራ ገበያው እንዳይገቡና የዜጎችን የሥራ ዕድል እንዳያጠቡ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እና ከታኅሣሥ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውን መመሪያ ከአዲሱ የአዋጅ ሥልጣን (አዋጅ ቁጥር 1156/2011) ጋር እንዲጣጣም እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
tigTIG
Scroll to Top