Mols.gov.et

News

News

በክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ …

በክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጨባጭ፣ ተስፋ ሰጪና አዳጊ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል
በሥራ ዕድል ፈጠራ መስኩ ያለውን ውዝፍ፣ አሁናዊ እና የመጪውን ጊዜ ሀገራዊ ፍላጎት መመለስ በዘርፉ ተግባራዊ የተደረገው ፎርም ዋና ማጠንጠኛ ነው።
በዚህ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተቀርፆ ወደ ሼል እንዲገባ የተደረገው “ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ” ስትራቴጂ፣ ዛሬ ላይ በሥራ ዕድል ፈጠራ ስነምዳር ውስጥ ተጨባጭ፣ ተስፋ ሰጪና አዳጊ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል።
በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ፣ ከ2.6 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል።
የሥራ ዕድል ፈጠራውን በዘርፍ ስንመለከተው፤ የአገልግሎት ዘርፉ የ40.5 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚነቱን ሲመራ፣ የግብርናው ዘርፍ 37.5 በመቶ እና ቀሪው 22 በመቶ የሚሆነው የሥራ ዕድል በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠረ ነው።
ከተፈጠረው አጠቃላይ የሥራ ዕድል ውስጥም 53 በመቶው በከተማ አካባቢዎች ሲሆን፣ ቀሪው 47 በመቶው ደግሞ በገጠር ለሚኖሩ ዜጎች የተመቻቸ ነው። ይህ ስርጭት በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኙ ሥራ ፈላጊዎችን ተደራሽ ለማድረግ በመንግስት የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ማሳያ ነው።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን በፈጠራና በፍትነት በማከናወን ከዕድገት ተኮር ዘርፎች ጋር ለማስተሳሰር በየደረጃው የተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረትና ርብርብ፣ ለዚህ ታላቅ ውጤት መገኘት የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል።
ለዜጎች ሰፋፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማሳደግና የኢንተርፕሪነርሺፕ ምህዳሩን በማስፋት፣ ዜጎች የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ አቋቁመው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ፤ የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለሀገራዊው የድህነት ቅነሳ ጉዞ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው።

Read More Âť
News

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚካሄደው ድጋፍና ክትትል …

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚካሄደው ድጋፍና ክትትል የዜጎችን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ተገለፀ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የድጋፍና ክትትል ቡድን በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የተከናወኑ የሥራና ሥራ ሥምሪት፣ የክህሎት ልማት፣ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳዮች እና የተቋም ግንባታ ተግባራትን ላይ ጠለቅ ያለ የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡
የድጋፍና ክትትል ቡድኑን የመሩት የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ አዝመራ ከበደ፤ በክልሉ ተሞክሮ የሚወሰድባቸው አበረታች ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን መመልከት ችለናል ብለዋል፡፡
በክልሉ በክህሎት ልማት ዘርፍ የተቀረጹ አዳዲስ እሳቤዎች ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረገው ጥረት አድንቀው በተለይ ኢንተርፕራይዞች ለመደገፍ የሚደረገው የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ሥራ፣ በተጨባጭ ውጤት እየታየበት መሆኑ በመስክ ምልከታው መረጋገጡን ጠቁመዋል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር በኮሪደር ልማት እና በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮች ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ የሚገኙ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ የተቀረጹ እሳቤዎች ወደ መሬት ለማውረድ የተጀመሩ ጥረቶች አሰሪም ሰራተኛውም ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡
ቡድኑ በቆይታው ጠንካራ ጎኖችን ተጠናክረው አንዲቀጥሉ ከማበረታታት ባለፈ፣ በሂደቱ የታዩ ክፍተቶች እንዲታረሙና ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አመላክቷል፡፡
ይህ የድጋፍና ክትትል ሥራ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑና የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ በሚያስችል መንግድ ለመተግበር ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንም የክልሉ የዘርፉ ኃለፊዎች ገልጸዋል።

Read More Âť
News

ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን …

ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ ነው – ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ 11ኛውን የሕብረት የስምምነት ተፈራርመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
‎‎
የአሠሪና ሠራተኛ መልካም ግንኙነት መኖሩ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻል የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዋነኛው መሣሪያ መሆኑንም አፅንዖት አንስተዋል።
‎በዕለቱ የተፈረመው የሕብረት ስምምነትም በአየር መንገዱ አመራርና በሠራተኛው መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥና ለተቋሙ ዘላቂ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አመላክተዋል፡፡
‎
ይህ ዓይነቱ ስምምነት በሚኒስቴሩ የታለመውን ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት የመገንባት ራዕይ በተግባር የሚያሳይ ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
‎
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ የሕብረት ስምምነቱ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ቀጣይነት ያለው ስኬት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ገልፀዋል።
የሕብረት ስምምነቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዕድገት በማፋጠን የሠራተኞችን ጥቅም በዘላቂነት የሚያስከብር መሆኑንም አብራርተዋል።

Read More Âť
News

ስምምነቱ በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት…

ስምምነቱ በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ኢንስቲትዩቱ አስታወቀ
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር፤ ስምምነቱ ኢንስቲትዩቱ ከቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን በማሻሻል በኩል ትርጉም ያለው ስራ እንዲሰራ ዕድል የሚፈጥርና በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ገልፀዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈቱ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች በኢንስቲትዩቱ እንደሚሰሩም አመላክተዋል።
ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ችግር ፈቺ የሆኑ ተኪ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት በትኩረት እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፤ የቡና ጥራትን በመጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የክህሎት ስልጠናዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ካለው የማሰልጠን፣ የፈጠራ እና የምርምር ሥራዎች አቅም አንጻር አብሮ መስራቱ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የያዛቸውን ዕቅዶች ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ነው ያመላከቱት። መረጃው የኢኒስቲትዪቱ ነው።

Read More Âť
News

የኢትዮ ኮደርስ ሰልጣኞች የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሥራ ዕድል ተጠቀሚ መሆን ጀመሩ!

የኢትዮ ኮደርስ ሰልጣኞች የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሥራ ዕድል ተጠቀሚ መሆን ጀመሩ!
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከ200ሺ በላይ ወጣቶች እና የመንግስት ስራተኞች ተመዝግበው ከ157ሺ በላይ ዜጎች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መውሰዳቸውን ተገለፀ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የተጀመረው የ 5 ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ወጣቶች የዲጂታል ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም አብራርተዋል።
ሰልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ ከማግኘት ባለፈ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት የሥራ እድል ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውንም ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂን ለማሳካት ሀገራችን የምታደርገው ጉዞ አካል ሲሆን በሦስት ኣመታት ውስጥ ሀገራችንን በዲጂታሉ ዓለም ተወዳዳሪ ማድረግ የሚችሉ 5ሚሊዮን ሰዎችን ማብቃትን ዓላማው አድርጎ እየተተገበረ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

Read More Âť
News

የሰው ልጅን የፈጠራ ችሎታ ከቴክኖሎጂ ጋር ማጣመር

የሰው ልጅን የፈጠራ ችሎታ ከቴክኖሎጂ ጋር ማጣመር
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ሳምንታዊ የጥናትና ምርምር ሴሚናር ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘ በአራተኛው (4.0) እና በአምስተኛው(5.0) የኢንዱስትሪ አብዮቶች፣ በኢንዱስትሪ ሽግግርና በምዘና ሥርዓት ውጤታማነት ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ሪፖርት እና ዕቅድ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ ላይ የቀረበው የመጀመሪያው የጥናት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ዓለም አቀፉ የኢንዱስትሪ አብዮት ከዲጂታላይዜሽን እና ከአውቶሜሽን ባለፈ የሰውን ልጅ የፈጠራ ችሎታ ከማሽኖች ጥምረት ጋር ወደሚያገናኘው አዲሱ ኢንዱስትሪ አብዮት 5.0 እየተሸጋገረ ይገኛል። ይህ ለውጥ በተለይም በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች አዳዲስና ዘመናዊ የክህሎት ዓይነቶችን እንዲላበሱ የሚያስገድድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ማሽኖች ያለ ሰው ንክኪ እንዲግባቡና ራሳቸውን ችለው ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያደርግ ሲሆን አምስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ደ ደግሞ ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ የመፍጠር አቅም እንዲያግዝ እንጂ እንዲተካው የማይፈለግበት ሥርዓት ነው።
ይህ አዲሱ አብዮት ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና ኢንዱስትሪዎች በችግር ጊዜ በቀላሉ የማይወድቁበትን ጥንካሬ መገንባት ላይ ትኩረት ያደርጋል።
ሆኖም አሁን ያለው የሀገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ-ትምህርት አሁንም በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ቴክኖሎጂዎች ላይ ገና እየተንደረደረ መሆኑና በዲጂታል ፋሽን ንድፍ፣ በስማርት ማምረቻ እና በዘላቂነት ረገድ ሰፊ የክህሎት ክፍተት መኖሩ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ሰልጣኞች ማሽኖችን ከማንቀሳቀስ ባለፈ የፈጠራ አስተሳሰብ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ጠንቅቀው ማወቅ እንዳለባቸው ጥናቱ አሳይቷል።
ለዚህም እንደ መፍትሄ የቀረቡት ምክረ-ሀሳቦች የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻል፣ ቴክኖሎጂ በየጊዜው የሚቀየር በመሆኑ የዕድሜ ልክ ትምህርት ግንዛቤን ማስረጽ፣ የመንግስትና የኢንዱስትሪ ትብብርን ማጠናከር፣ እንዲሁም ማሽኖች ሊተኳቸው የማይችሏቸውን የሰው ልጅ ልዩ ባህሪያት (Soft Skills) ማዳበር የሚሉ ናቸው። ይህም ሰልጣኞችን ከቀጣሪነት ባለፈ የቴክኖሎጂ መሪ እና ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል።
በተጨማሪም በሴሚናሩ ማጠናቀቂያ ላይ በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የምዘና ልምዶች እና ምሩቃን ብቃት ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ የሚያሳይ የጥናት ዕቅድ (Proposal) ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። ይህ የጥናት ዕቅድ ወደፊት በዘርፉ ላይ የሚታዩ የአፈጻጸም እና የጥራት ችግሮችን ለመፍታት እንደ ዋነኛ ግብዓት ያገለግላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል፡፡

Read More Âť
News

የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ቅንጅት..

የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ቅንጅት፤ ለተወዳዳሪ የሰው ኃይል ልማት!
ትውልድን ለመጪው ዘመን ማዘጋጀትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱን ማረጋገጥ የጊዜው አጣዳፊ ጥያቄ ነው።
ይህ በተሟላ ደረጃ እውን እንዲሆን በትምህርትና ሥልጠና ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅት መጠናከር የሰው ኃይል ልማታችን ከሥራ ገበያው ፍላጎት ጋር እንድናጣጣምና በሥራ ዕድል ፈጠራና በፈጠራ ሥነ-ምህዳሩ ላይ የሚኖረው አበርክቶ እንዲጎለብት ያደርጋል።
ላለፈው አንድ ዓመት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን የተቋም በህል ግንባታ ሥራችን አካል የሆነው ወርሃዊ “የማለዳ ውይይት” መርሃ-ግብር በዛሬው እለት በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ተቋማት መካከል ስትራቴጂካዊና እሴት-አካይ ቅንጅት መፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ምክክር ተካሂዷል።
ይህ መድረክ ተቋማቱ ለየብቻ ከመጓዝ ወጥተው ለጋራ ሀገራዊ ግብ እንዲሰናሰሉ የሚያስችል አዲስ የትብብር ምዕራፍ ከፍቷል።
በዚህም ከእውቀትና ክህሎት ባለፈ፣ ችግርን ወደ ዕድል የሚቀይሩና ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬ ያላቸው፤ በጠንካራ ሥነ-ምግባር የታነጹ፣ አቋራጭ መንገድን የማይሹና ለሀገራዊ ውጤት የሚተጉ፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑና በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት የሰው ኃይል ልማታችን ዋነኛ ማጠንጠኛ መሆን ይኖርበታል፡፡
ከምክክሩ ጎን ለጎን የመድረኩ ተሣታፊዎች የኢትዮጵያን የሥራ ገበያ ሥርዓት እና የመንግስት አገልግሎት የፈጠራና የማሻሻያ ማዕከን በመጎብኘት በቀጣይ ተቀናጅቶ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተቀራርቦ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል።

Read More Âť
News

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ወደ ፈጠራና የጥበብ መናኻሪያነት የሚያሸጋግረው

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ወደ ፈጠራና የጥበብ መናኻሪያነት የሚያሸጋግረው የዘርፉ እሳቤ……
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከዚህ ቀደም የሚታወቁት በአጫጭር እና መደበኛ ፕሮግራም ያሰለጠኗቸውን ወጣቶች ሰርተፍኬት ሰጥተው በመሸኘት ነበር ፡፡ አሁን ግን ይህንን የተለመደ አሰራር የሚቀይር አዲስ እሳቤ ተቀርጾ በዘርፉ ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል፡፡
እሳቤው ሰልጣኞች በኮሌጅ ቆይታቸው ከሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ጋር የሚስማማ ኢንተርፕራይዝ አቋቁመው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችል አዲስ እይታ ነው፡፡
በአሁን ወቀት ይህንን እሳቤ እውን ለማድረግ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሥራ ጀምረዋል፡፡ በዚህም ሰልጣኞች ስልጠና ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ 20% ቁጠባ እንዲቆጥቡ በማድረግ፣ ለሚመሰርቱት ኢንተርፕራይዝ መነሻ የሚሆን አቅም እንዲፈጥሩ እየተደረገ ይገኛል።
ከቴክኒካዊ ስልጠናው ጎን ለጎን በቀጣይ የኢንተርፕራይዝ ባለቤት የሚሆኑ ወጣቶችን ስኬታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የኢንተርፕሪነርሺፕ እሳቤን ለመላበስ የሚያስችላቸውን ስልጠናም ከተቋማቱ ያገኛሉ፡፡
ኮሌጆች ያሏቸውን ማሽኖች ተጠቅመው እያመረቱ እንዲሰለጥኑ፣ እየሰለጠኑ እንዲያመርቱ የተቀመጠው አቅጣጫ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን ብቃትና ተወዳዳሪነት የሚያልቅ ሌላኛው የአዲሱ የዘርፉ እሳቤ ገፅታ ነው፡፡
የቴክነኒክና ሙያ ተቋማት ጥራት ያለው ስልጠና አግኝተው፣ የኢንተርፕሪነርሺፕን ባህሪ ተላብሰው፣ በኮሌጆቹ ውስጥ በሚቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች እጃቸውን፣ ልባቸውንና አእምሯቸውን ቃኝተውና ኢንተርፕራይዝ መስርተው የሚወጡ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎች የሚወጡባቸው ተቋማት ናቸው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺና መፍትሄ አመንጪ ዜጎች በስፋት የሚፈሩባቸው ማዕከላት እንዲሆኑ ማስቻል፣ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ስብራት የሚጠግኑ ባለወርቅ እጆች የሚፈጠሩባቸውና ሀገርን የሚያልቁ ኩባንያዎች የሚፈለፈሉባቸው የፈጠራና የጥበብ መናኻሪያነታቸውን ዕውን ማድረግ ደግሞ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተቀረፀው አዲሱ የክህሎት ልማት እሳቤ አዲሱ መዳረሻ ግብ ነው!

Read More Âť
News

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ2,300 በላይ ባለሙያዎችን ለሥራ ገበያው በማቅረብ

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ2,300 በላይ ባለሙያዎችን ለሥራ ገበያው በማቅረብ የዘርፉን ተወዳዳሪነት እያረጋገጠ ነው
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚያችን እምቅ አቅም ያለው ቢሆን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እና የሀገር በቀል ምግቦቻችን በዘመናዊው መስተንግዶ ውስጥ በሚፈለገው መጠን አለመካተታቸው በዘርፉ ገቢና ተወዳዳሪነት ላይ የራሱ የሆነ ጫና ሲፈጥር ቆይቷል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ ተቋማዊ አሰራሩን በ ISO-21001:2018 ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ በማደራጀት ሰፊ የክህሎት ማበልጸጊያ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ስድስት ወራት በዳቦና ኬክ ዝግጅት፣ በኩሊነሪ አርት፣ በምግብና መጠጥ ቁጥጥርና መስተንግዶ ዘርፎች ጥራት ያለው ተከታታይ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።
ከዚህም በተጨማሪ የሀገር በቀል ምግቦችን በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት ወደ ሆቴሎች የንግድ ስርአት (Menu) የማስገባት ስትራቴጂካዊ ሥራን በልዩ ትኩረት እሠራ ይገኛል።
በዚህም ባለፉት 6 ወራት ብቻ 2,346 አዳዲስና ነባር ባለሙያዎችን በክህሎት ማብቃት የቻለ ሲሆን፣ ይህም የዕቅዱን 67 በመቶ መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ ስልጠና ባለሙያዎቹ በተሻለ ደመወዝ እንዲቀጠሩና የሆቴሎች አገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል መንገድ ከፍቷል።
በተመሳሳይ፣ ኩሪፍቱ ሪዞርትና ሞናርክ ሆቴልን ጨምሮ ስድስት የሚሆኑ ሆቴሎች የኢንስቲትዩቱን የጥናት ውጤት መሠረት በማድረግ ባህላዊ ምግቦችን በሜኗቸው አካተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ይህም ባህላዊ ምግብና መጠጦቻችንን ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማስተዋወቅና የገበያ ዕድልን ለማስፋት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፡፡

Read More Âť
News

ከስደት ተመላሽ ዜጎችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ ወደ ሥራ

ከስደት ተመላሽ ዜጎችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ ወደ ሥራ የማስገባት ተግባር በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለፀ
‹‹አካታችነት›› በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ የዋለው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡
በዚሁ መሰረት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሰጡ ስልጠናዎች ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ወጣቶችን ስደተኞችንና ሌሎችም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በእኩል ተደራሽ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይጠበቃል፡፡
የትኩረት አቅጣጫውን ወደ ተግባር ለመለወጥ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም በአስተዳደሩ ሥራና ክህሎት ቢሮ እንዲሁም የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት በሥደተኞች ላይ በሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተጎብኝተዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ ወጣቶችንና ተመላሾችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ ይገኛል።
ስልጠናው ወጣቶች በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ እንዲሰማሩና የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ እንዲመሰርቱ የሚያስችል ሲሆን ይህም ከጥገኝነት መንፈስ ተላቀው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እድል የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ስደትን በዘላቂነት ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተገልጿል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው በድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እየተከናወነ ያለው ተግባር መልካም መሆኑን ገልጸው በተለይም ወጣቶች የሚያገኙትን እውቀት ወደ ገቢ ምንጭ በመቀየር የተሻለ ህይወት እንዲመሩ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ለሌሎች አካባቢዎችም አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። መረጃው የድሬዳዋ ሥራና ክህሎት ቢሮ ነው፡፡

Read More Âť
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
oroORO
Scroll to Top