Mols.gov.et

mols mols

News

ፕሮጀክቱ ብቁ እና ተወዳዳሪ ሰልጣኞችን ለሥራ ገበያው ለማቅረብ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

ፕሮጀክቱ ብቁ እና ተወዳዳሪ ሰልጣኞችን ለሥራ ገበያው ለማቅረብ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ትምህርትና ስልጠና ለሥራ ሥምሪት ፕሮጀከት (EASE Project) የአፈጻጸም ግምገማ እና ስልጠና መድረክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተውጣጡ አስተባባሪዎች እና የሥራ ቦታ ደህንነት ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ሐፍቶም ገ/እግዚያብሔር(ረ/ፕሮፌሰር)፣ ፕሮጀክቱ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በሥራ ገበያው ብቁ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ሰልጣኞች እንዲያፈሩ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ፕሮጀክቱ የሥራ ጥራት ላይ እንደሚያተኩር የተጠቆመ ሲሆን አዳዲስ የሚጀመሩ እና የሚሻሻሉ ፕሮግራሞች ላይ ውጤታማ አፈጻጸም እንዲመዘገብ የጋራ አረዳድ ለመፍጠር መድረኩ መዘጋጀቱ ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ወደ ሥራ ሥምሪቱ የሚገቡ ሰልጣኞች የሥራ ቦታ ደህንነት የሚያረጋግጥ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝም አስተባባሪው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ እና በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስፈጻሚነት ሚኒስቴር መ/ቤቱን ጨምሮ በ24 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

Read More Âť
News

ኢንስቲትዩቱ ከአልጀሪያ መንግስት የተገኘ ስኮላርሺፕ ተጠቃሚ ለሆኑ …

ኢንስቲትዩቱ ከአልጀሪያ መንግስት የተገኘ ስኮላርሺፕ ተጠቃሚ ለሆኑ የደረጃ 6(መጀመሪያ ዲግሪ) ሰልጣኞች የሽኝት መርሀግብር አካሄደ።
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የስልጠናና አቅም ግንባታ ም/ዋና ዳይሬክተር ሐፍቶም ገ/እግዚአብሔር (ረ/ፕሮፌሰር) ይህ የግለሰቦች ትምህርት ጉዳይ ብቻ አይደለም አገርን በዓለምአቀፍ መድረክ የመወከል፣ ለዘርፉ ተጨማሪ አቅም የመፍጠር ጉዳይ ነው ብለዋል።
የአልጀሪያ ህዝብና መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያበረከቱት ይህ ስኮላርሺፕ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቅርብ ክትትል እውን መሆን ችሏል ያሉት ሐፍቶም (ረ/ፕሮፌሰር) ለዚህም ክብትር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ላደረጉት አመራር ሰጪነት ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል።
ም/ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢንስቲትዩቱ ለአገራችን የግብ ስኬት ቁልፍ ዘርፍ ለሆነው የክህሎት ልማት የመሪነት ሚና የሚወጣመሆኑን ገልጸው በዚህ ዕድል የሚጠቀሙ ወጣቶ ሲመለሱ የሚጨምሩት አቅም ብዙ ነው ብለዋል።
ተማሪ ታምራት ወንድምኩን እና ተማሪ ትህትና ለተሰጣቸው እድል አመስግነው በመጀመሪያ ኢንስቲትዩቱን መርጠው መግባታቸው በብዙ መንገድ እንደጠቀማቸው ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ፣ ውጤታማ ተማሪዎች ሆነን አገራችን የሰጠችንን አደራ በብቃት ተወጥተን ህዝባችንን ለመጥቀም ቃል እንገባለን ብለዋል።
በመጨረሻም የኢንስቲትዩቱ የስልጠናና አቅምግንባታ ም/ዋና ዳይሬክተር ሐፍቶም ገ/እግዚአብሔር (ረ/ፕሮፌሰር) ከአደራ ጋር የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በክብር አስረክበዋል@FTVT

Read More Âť
News

መሶብ፡ የእፎይታ ማዕከል

መሶብ፡ የእፎይታ ማዕከል

አቶ ብሩክ በሚሠራበት ተቋም ውስጥ ተቀጥረው ለሚያገለግሉ የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ ለማውጣት፣ ለማሳደስና ለማሰረዝ በየጊዜው አገልግሎቱን ይሰጡ ወደነበሩ ተቋማት ይመላለስ እንደነበረ ይናገራል፡፡
ወ/ሮ ትብለፅም በተመሳሳይ በምትሠራበት ካምፓኒ ከ 200 በላይ ቻይናውያን መኖራቸውን ትናገራለች፡፡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በሌለበት ሁኔታ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳይ ማስፈፅም እጅግ ፈታኝ መሆኑን ትገልፃለች፡፡
አቶ አብዲማ ደግሞ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነት ቡድን መሪ ናቸው ፡፡ እሳቸውም በዩኒቨርሲቲያቸው ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ ህንዳውያንን የሥራ ፈቃድ ጉዳይ ለማስፈፀም ለበርካታ ዓመታት ወደ አዲስ አበባ ይመላለሱ እንደነበረ በማስታወስ የሚወስድባቸው የተራዘመ ጊዜ ለብዙ ችግርና እንግልት ይዳርጋቸው እንደነበረም ይናገራሉ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት አገልግሎቱ የሚሰጠው ማኑዋል በሆነ መልኩ ስለነበር ፋይል መፈለግ፣ ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል በነበረው ምልልስ ሳቢያ አንድን ጉዳይ ለማስፈፀም ከሁለት ሳምንት በላይ ይፈጅባቸው እንደነበር ሦስቱም ተገልጋዮች ያስታውሳሉ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቋቋመ በኋላ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (E-LMIS) አማካኝነት የሚሰጥ መሆኑ በተወሰነም ደረጃ ሥራውን አቀላጥፎት እንደነበር የሚገልፁት ተገልጋዮች ነገር ግን የተወሰኑ አገልግሎቶች በተለያየ ቦታ የሚሰጡ መሆናቸውበአሠራር ፍጥነት ላይ የራሱ የሆነ ተፅ ዕኖ እንደነበረው ይናገራሉ፡፡
ዛሬ ሦስቱም ባለጉዳዮች ቅልጥፍናን ከፍጥነት ጋር አጣምሮ በያዘው የ‹‹መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት›› ተገኝተዋል፡፡
ከጋምቤላ ከአንድ ቀን በፊት መምጣታቸውን የሚናገሩት አቶ አብዲማ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ዲጂታል በሆነ መልኩ በመጫናቸው ከግማሽ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን ማጠናቀቃቸውን ይገልፃሉ፡፡
‹‹ከዓመታት በፊት የነበረውን ውጣውረድ ለሚያውቅ ሰው ይህ በእጅጉ ህልም ነው›› የሚሉት አቶ አብዲማ አሠራሩ ወደ ዲጂታል ከማደጉ በላይ የማዕከሉ ባለሙያዎች ብቃትና ሥነ ምግባርም አገልግሎቱን የበለጠ ምቹ እንዳደረገው ይናገራሉ፡፡
‹‹እንደ እኔ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳይ ለሚያስፈፅም ሰው ፍጥነትና ቅልጥፍና በእጅጉ ወሳኝ ነው›› የምትለው ትብለፅ በመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በተገኘች በውሱን ደቂቃዎች ውስጥ ጉዳዩዋን ማጠናቀቅ መቻሏ ህይወቷን በእጅጉ እንዳቀለለውም ትናገራለች፡፡
‹‹ላለፉት ስምንት ዓመታት አንድን ጉዳይ ለማስፈፀም ለሳምንታትና ለወራት እመላለስ ነበር›› የሚለው አቶ ብሩክም በበኩሉ በመሶብ አንድ ማዕከል ያገኘው አገልግሎት ጉልበቱንና ጊዜውን በእጅጉ እንደቆጠበለት በፈገግታ ታጅቦ ይናገራል፡፡
በ‹‹መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት›› የተጀመረው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትልና ትኩረት እንደሚፈልግ የሚናገሩት ሦስቱም ባለጉዳዮች በቀጣይ ሁሉም መንግስታዊ ተቋማት የአገልግሎት ደረጃቸውን ለማሻሻል ‹‹መሶብ መልካም አርዓያ የሆነ ተቋም ነው ›› በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Read More Âť
News

በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አሰራር እንዲጠናከር በቅንጅት እየተሰራ ነው

በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አሰራር እንዲጠናከር በቅንጅት እየተሰራ ነው
በኦሮሚያ ክልል ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲጠናከር በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ላይ ያተኮረ ኤጀንሲዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዳማ አካሄዷል።
የቢሮ ሃላፊው አቶ አራርሶ ቢቂላ በወቅቱ እንደገለፁት፥ በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
በዚህም ከፀጥታና ፍትህ አካላት እንዲሁም በዘርፉ ከተሰማሩና በክልሉ ከሚሰሩ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት የኤጀንሲዎች ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ህገወጥ ስደት በዜጎች ህይወት ላይ እና በአገር ገጽታ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዜጎችም ህጋዊ መንገድ ብቻ መከተል እንዳለባቸው መክረዋል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አቢት ኤዳኦ በበኩላቸው፥ በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመግታት ለወጣቶች የግንዛቤ ማስረጽ ስራ እየተካሄደ ነው።
በተለይ ወደ ተለያዩ ሀገራት በደላሎች ተታለው በህገወጥ መንገድ የሚጓዙ ዜጎች ለአስከፊ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን እንዲገነዘቡ ከማድረግ አኳያ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን የሚያከናውኑ ኤጀንሲዎች ህጋዊ አሰራርን ተከትለው እንዲሰሩ በ21 ዞኖችና በ23 ከተሞች ላይ ክትትል፤ ድጋፍና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የስራ ስምሪትና የገበያ መረጃ ስርዓት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋንታዬ ታደሰ ናቸው።
በተለይ የፀጥታና ፍትህ አካላትን ጨምሮ ከጨፌ ኦሮሚያ፤ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት በህጋዊ መንገድ ከክልሉ 153 ሺህ ዜጎች ወደ ተለያዩ ሀገራት ለስራ መጓዛቸውንም አስታውሰዋል።
በመድረኩ ላይ ከተሳተፉ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ኤጄንሲዎች ተወካዮች መካከል አቶ ኢዘዲን አህመድ፣ በርካታ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት ለስራ በኤጀንሲያቸው በኩል መጓዛቸውን ተናግረዋል።
ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዜጎችም በህጋዊ መንገድ ብቻ በመጓዝ ከሚገጥማቸው አደጋ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው::

Read More Âť
News

ፕሮጀክቱ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አካል ሂደት ነው፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

ፕሮጀክቱ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አካል ሂደት ነው፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የተመረቱ ተኪ ምርት ቴክኖሎጂዎች ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ሙሉ ለሙሉ የተመረተ ኢንዳክሽን ሞተር፣ ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጀር እና ስማርት ፖልን ጨምሮ የተለያዩ ዲጂታል መተግበሪያዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በምንሰራቸው ሥራዎች ውስጥ ሁሉ በርካታ ማነቆዎች አሉ፡፡
እነዚህ ችግሮችን ስናውቃቸው፣ ስንተባበርና ስንተጋገዝ ወደ ዕድል ይቀየራሉ፡፡ የዚህ አይነት ፕሮጀክቶች የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አካል ሂደት ነው ብለዋል።
ያለንበት የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ ይንን ተገንዝቦ እዚህ ላይ የሚሰራ ተቋም ረዥም ርቀት መሄድና የሀገር የጀርባ አጥንት ሆኖ ማገልገል እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ትልቅ ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም እንደሆነ ያመላከቱት ክብርት ሚኒስትር ይህን ተልዕኮውን በመደመር እሳቤ እውን እንዳደረጉትም ጠቁመዋል፡፡
ተኪ ምርቶቹ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ቴክኖሎጂዎቻቸውን እንዲያጎለብቱና ለገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል የተቀረፀው የ‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› መርሃ ግብር ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› ላለፉት ሁለት አመታት በጣም ትልልቅ ሥራዎች የተሠሩበት፤ በርካታ ቴክኖሎጂዎች የመነጩበትና ለሀገር የጀርባ አጥንት የሆኑ ለኢኮኖሚያዊ አስተዋጾ ያላቸው ሥራዎች የተሠሩበት መሆኑንም ክብርት ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡
መሰል ቴክኖሎጂዎች ለበርካታ ዜጎች ሥራ ዕድል መፍጠሪያ አማራጭ ሆነው የሚያገለግሉ ከመሆኑ በላይ የተለያዩ አምራች ኢንተርፕራይዞችም ሥራቸውን በቀላሉ በቴክኖሎጂ ታግዘው ማከናወን እንዲችሉ ከማድረግ አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡
ቴክኖሎጂዎቹ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን በማሳደግ የሀገርን ኢኮኖሚ የመገንባት አቅም ያላቸው በመሆኑ ለሚፈጥሩ አእምሮዎችና ለሚሠሩ እጆች ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግም ክብርት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ውጤት መገኘት እንደ ዘርፋቸው እንደ ሙያቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Read More Âť
News

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮችን ከክርክር ይልቅ ወደ ምክክር ለመቀየር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ።

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮችን ከክርክር ይልቅ ወደ ምክክር ለመቀየር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ።
የፌዴራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የወሳኝ ቦርድ አባላት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የልምድ ልውውጥ አካሂደዋል ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በአሠሪና ሠራተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ ክርክር ከመግባታቸው በፊት በስምምነት ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ በመድረኩ ተገልጿል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ወሳኝ የሆኑ የህግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸው እና መከለሳቸው የተገለፀ ሲሆን የአነስተኛ ደመዎዝ ቦርድ ደንብ እንዲዘጋጅ መደረጉ ፣ የአሠሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ አሰራርና አደረጃጀት ሥነ ሥርአት ማንዋል እና የአሠሪ ሠራተኛ ቋሚ አማካሪ ቦርድ የቴክኒክ ኮሚቴ ጋይድላይን መዘጋጀቱም ተብራርቷል፡፡
በአፈጻፀም ሂደት ውስጥም ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ በመድረኩ የተነሳ ሲሆን የወሳኝ ቦርድ እና አማካሪ ቦርድ የመስክ ክትትልና ድጋፍ የማጠናከር፣ የሥራ ክርክርን የሚቀንሱ ምርታማነትን የሚጨምሩ ሂደቱን በግብአት መደገፍና ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን የመከታተል ሥራዎች መሰራታቸውም ተብራርቷል፡፡
የፌደራል ወሳኝ ቦርድ የችሎት ስታንዳርድ እና የዲጂታል አሰራር ሂደትን ከባቢ የተሻለ ማድረግ በቀጣይ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚሰሩ ቁልፍ ተግባራት ሆነው ተቀምጠዋል።

Read More Âť
News

የሥራ ሥምሪት አፈጻጸም

የሥራ ሥምሪት አፈጻጸም
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የዘርፉን የመጀመሪያው እሩብ ዓመት አፈጻጸም ከክልል እና ከተማ አስተዳድር የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በበይነ መረብ ገምግመዋል፡፡
የግምገማና ውይይት መርሃ ግብሩ አላማ በዋናነት በሩብ ዓመቱ የተቀመጡ ግቦች ከማሳካት አኳያ የተገኙ ስኬቶች ለማስፋት እና በጉድለት የታዩ አፈጻጸሞች በተያዘው እሩብ ዓመት እቅድ ተካተው እንዲተገበሩ ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በግምገማ መድረኩ በዋናነት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት አፈጻጸም ማላቅ፣ እሴት ሰንሰለትን የተከተለ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሥራ ሥምሪት ማሳለጫ የሆኑት የሥራ ማዕከላት ሪፎርም እና ዘላቂ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩት የቤተሰብ እና የማህበረስብ ቢዝነስ ማስፋፋት ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና ከፍተኛ የማደግ አለኝታ ያላቸውን ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ፣ በኢመደበኛ ንግድ የተሰማሩት ወደ መደበኛ ንግድ ዘርፍ እንዲገቡ ማድረግ እንዲሁም የኢንተርፕራይዞች የገበያ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በድጅታል ስርዓት እንዲመዘገቡ ማድረግ ልዩ የአመራር ትኩረት የሚሹ የዘርፉ ተግባራት መሆናቸውንም ተገልጿል፡፡

Read More Âť
News

ከሞተር ሳይክል ማጠብ እስከ ተሽከርካሪ አስመጪነት …

ከሞተር ሳይክል ማጠብ እስከ ተሽከርካሪ አስመጪነት …
የምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ከተማ ተወላጅ የሆነው ወጣት ሳዳም አብዳ ከ12 ዓመታት በፊት በ10 ብር ክፍያ ነበር የሞተር እጥበት ስራውን የጀመረው።
በወቅቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ማሕበር በመደራጀት ባገኘው 5 ሺህ ብር ስራውን የጀመረው ወጣቱ፣ በትጋት በመስራት ወደ ተሽከርካሪና ሞተር ሳይክል አስመጪነት መሸጋገሩን ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።
በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በመግባት በአውቶሞቲቭ ስልጠና በከፍተኛ ውጤት መመረቁን የሚገልጸው ወጣት ሳዳም፣ ትልቅ ዓላማ ሰንቆ በመነሳት ከምርቃቱ በኋላ በጊኒር ከተማ የሞተር ሳይክል እጥበት ስራውን እንደጀመረ አስታውሷል።
ቀስ በቀስም ስራውን ሞተር ሳይክል ወደ መጠገን በማሳደግ ከዓመታት በኋላ የሞተር መለዋወጫና አሮጌ ሞተር ሽያጭ ስራ ላይ በመሰማራትና በትጋት በመስራት ወደ ተሽከርካሪ መለዋወጫ መሸጫ ማሸጋገሩን ገልጿል።
በዚህም በጥቂት ዓመታት ወስጥ የተለያዩ ዘመናዊ ሞተር ሳይክሎችን በማምጣት ሽያጭ እንደጀመረ በመግለጽ፣ በሂደትም ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ መለዋወጫና ሞተር ሳይክሎችን ከውጭ ሀገር በስፋት እያመጣ መሸጥ መጀመሩን ጠቁሟል።
ከ5 ዓመታት በፊት ጀምሮ ከሞተር ሳይክል አስመጭነት በተጨማሪ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት የንግድ ሥራውን እንዳሳደገና በጊኒር ከተማ የጀመረውን ስራ በተለያዩ ሰባት ከተሞች ላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጸው።
አሁን ላይ ከራሱ አልፎ ከ230 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል እንዲሁም በጊዜያዊነት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችሏል።
በቀጣይም ስራውን በማሳደግ ወደ ተሽከርካሪ ማምረቻነት ለመሻገር ወጥኖ እየሰራ መሆኑን ይናገራል።
ማንም ሰው ዓላማውን ማሳካት ከፈለገ የስራ ባህሉን ማሳደግ፣ ስራን ማክበር፣ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀምና የተግባር ሰው ሊሆን እንደሚገባም ሐሳቡን አጋርቷል።
ወጣቱ ድጋፍ ላደረገለት ማሕበረሰብ የምስጋና መርሐ ግብር ያዘጋጀ ሲሆን÷ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙሀመድ አብዱልቃድር አቶ ሳዳም ለወጣቱ ምሳሌ የሚሆንና ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግለት አረጋግጠዋል።
ከዚህ ቀደም ለተሽከርካሪ መገጣጠሚያ መክፈት የሚያስችል 5 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ቦታ ከከተማ አስተዳደሩ በማግኘት ስራውን ለመጀመር የግንባታ ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
አቶ ሳዳም በታማኝ ግብር ከፋይነት 900 ሚሊየን ብር በመክፈል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተከታታይ ሦስት ዓመታት እውቅና ማግኘቱን ጠቅሶ የዘገበው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው፡፡

Read More Âť
News

የተገልጋዮችን እርካታ 95 ከመቶ በላይ ማድረስ ያስቻለው ማዕከል

የተገልጋዮችን እርካታ 95 ከመቶ በላይ ማድረስ ያስቻለው ማዕከል
ቴክኖሎጂ የሥራ ቅልጥፍናን፣ ምርታማነትንና ውጤታማነት ያሳድጋል፡፡ ፈጠራና ፍጥነትን ማዕከል ባደረገው አቅጣጫ መንግስት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለዜጎች ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ፣ ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ አገልግሎቶቹን በቴክኖሎጂ አስተሳስሮ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡
በፌዴራል ደረጃ ባለው ማዕክል 23 ተቋማት አገልግሎታቸውን በማዕከሉ አስገብተዋል፡፡ ከእነዚ ተቋማት መካከል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚገኝ ሲሆን የውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሥራ ፈቃድ እና የዲጂታል ኢንተርፕራይዝ ምስረታ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች በማዕከሉ እየተሰጡ ይገኛል፡፡
የ100 ቀናት የሥራ አፈፃፀም ላይ እንደተመላከተው በማዕከሉ 180 አገልግሎቶች ባሳለፍነው መቶ ቀናቶች ብቻ ተሰጥተዋል፡፡ ከ79 ሺህ በላይ ተገልጋዮችም በማዕከሉ አገልግሎት እንዳገኙና በማዕከሉ አገልግሎት ካገኙ ዜጎች በተወሰደ መረጃም የእርካታ ደረጃቸው 95 በመቶ በላይ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ የተሰጡ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህ በሰጡት ማብራሪያ የመንግስት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት በቴክኖሎጂ አግዞ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግና ብልሹ አሰራርን ለመቀነስ መንግስት በልዩ ትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
በፌዴራል ደረጃ ወደ ሥራ ከገባው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በተጨማሪ ወደ ክልሎች እንዲሰፋ አቅጣጫ ተቀምጦ በዚህም በተለያዩ የክልል ከተሞች ማዕከሉን ወደ ሥራ ማስገባት እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡
መሶብ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን በዘላቂነት ከመፍታት፣ ብልሹ አሰራርን ከማስቀረት እና የተገልጋይ እርካታን ከማሳደግ አኳያ ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ያብራሩት ክቡር አቶ አደም ፋራህ እስከ ሰኔ 2018 ድረስ ማዕከላቱን 100 ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡
ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም ፤

Read More Âť
News

የዲጅታልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ነው። ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

የዲጅታልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ነው።
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ፣ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት በተሰጠው ትኩረት የዲጂታልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ4ኛው ዙር ሰመር ካምፕ በሳይበር ደህንነትና ተያያዥ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶችን አስመርቋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በዲጂታል ዘመን ወቅቱን የዋጀ በክህሎት መር እውቀት የሠለጠነ ዜጋን ማፍራት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሳይበር ደህንነትና ዘመኑ የሚፈልገውን የቴክኖሎጂ እውቀት የታጠቁ ወጣቶችን በተከታታይ የማሰልጠንና የማሰማራት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት በሰው ኃብት ልማት በተለይ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች አቅም ለማጎልበት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የሳይበር ጥቃትን በብቃት የሚከላከልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ህልምን የሚያሳካ የዲጂታል አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በዲጂታል ዘርፉ ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል እያደረገች ላለው ሽግግር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የበቃ የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ዋና ዓላማ በዘርፉ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች ክህሎት በማሳደግና በዘርፉ ለሀገር የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ወቅቱን የሚመጥን ብቁ፤ ዕውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የሳይበር ታለንት ስልጠና አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስር በመፍጠርና በተቋሙ የሚሰሩ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች እውቅና እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፈጠራ ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር የሚያግዝ የሥራ ፈጣሪዎች አቅም ማጎልበቻ ማዕከል ከፍቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል።
በዚህ በሰመር ካምፕ የፈጠራ ስራ ያላቸው ታዳጊዎች በማዕከሉ ውስጥ የፈጠራ ስራቸውን ማስፋትና ወደ ገበያ የሚያቀርቡበትን ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በሰመር ካምፑ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች በበኩላቸው በቆይታቸው የተለያዩ ክህሎቶች ማግኘታቸውን ገልጸው በቀጣይ ሀገራቸውን በዲጂታል ዘርፎች ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ወጣት አሌክሳንደር ሳሙኤል እንደተናገረው የኢ-ለርኒንግ ስርዓት ማበልጸጉን በማንሳት፥ የጀመረው ሥራ የትምህርት ስርዓቱን በዲጂታል ለማሳለጥ ዓላማ ያለው ነው ብሏል።
ሌላው ወጣት ኬና ቶልቻ በቆይታው በኤሮስፔስ ዘርፍ ስልጠና መውሰዱን በመግለፅ፥ በድሮን ኦፕሬሽን ላይ እውቀት መቅሰሙን ጠቁሟል።
ወጣት ባስሌል መስፍን በበኩሉ በሶፍትዌር ማበልፀግ ስልጠና እንድወሰደ ጠቅሶ፥ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የተጓዦችን ህዝብ ትራንስፖርት አጠቃቀም የሚያሳልጥ መተግበሪያ መስራታቸውን ገልጸዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው።

Read More Âť
The Minister Is answering questions live in zoomClick To join the live Meeting
+
en_USEN
Scroll to Top