የሀገራችን ዕድገት ትልቁ ምሰሶ ሠራተኛው ነው ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ
ሚያዝያ 30, 2026
የሀገራችን ዕድገት ትልቁ ምሰሶ ሠራተኛው ነው
ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
በኢትዮጵያ ለ51ኛ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ137ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) አስመልክቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዘንድሮው በዓል “የሠራተኛው መብት መከበር ለኢንዱስትሪ ሰላምና ለምርታማነት መሠረት ነው!” በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 23 ቀን በድምቀት የሚከበረውን የሜዴይ በዓል አስመልክቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን ለማስፈን በርካታ ሪፎርሞችን ማድረጉን ጠቁመው፣ አሰሪና ሠራተኛ ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አብራርተዋል።
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዜጎችን ደህንነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ጠቁመዋል።
መንግስት የሠራተኞችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው የሥራ ላይ ደህንነትን ለመጠበቅና አደጋዎችን ለመከላከል የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን(የኢሰማኮ) ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው የሠራተኛው መብት መከበር ለሀገር እድገትና ለምርታማነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚያደርገው አሰሪ፣ ሠራተኛና መንግስት በጋራና በትብብር የሚያከብሩት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሞገስ ቀኑን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የሠራተኛውን መብት የማያከብር አሰሪ ምረታማነቱን ከማሳደግ ይልቅ ጊዜውን በንትርክ ይጨርሳል ብለዋል፡፡
ይህንን ተገንዝበው በአሁኑ ወቅት በርካታ አሰሪዎች ለሠራተኞቻቸው ቅድሚያ በመስጠት አበረታች ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።
ከወዲሁ እንኳን ለአለም የሰራተኞች ቀን አደረሳችሁ!

