Mols.gov.et

ከንብ ትጋት የተቀሰመ ጣፋጭ ስኬት

ታህሳስ 25, 2024
ከንብ ትጋት የተቀሰመ ጣፋጭ ስኬት ነዋሪነቱ በድሬዳዋ ከተማ የሆነው አቶ አብዱልቃድር ሁሴን እብራሂም ከዓመታት በፊት ከተማረው ኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ጋር የተያያዘ ሥራ ላይ ነበር የተሰማራው፡፡ የሥራው ባህሪ ሆኖ ረጅም ሰዓት ተቀምጦ መቆየቱ የሚያመጣውን የሰውነት ክብደት እና ተያያዥ የጤና ችግሮች ለመከላከል በቀን የተወሰነ ሰዓት ጎንበስ ቀና ብሎ ሊሠራው የሚችለውን ሥራ ማሰብ ጀመረ፡፡ በቤተሰቦቹ ግቢ ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት በሃሳቡ ከመጡ ሥራ አይነቶች መካከልም ቀዳሚው ነበር፡፡ ሥራውን እንደ አካል ብቃት እንቅስቃሴም ጭምር በመውሰድ ቲማቲም፣ ጎመን ቃሪያ የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶችንና እንደ ብርቱካንና ሎሚ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን ማልማት ጀመረ፡፡ እንደ ቀላል የጀመረው ሥራ እያደገና እየተስፋፋ ሲሄድ ከቤተሰብ ፍጆታ አልፎ የገቢ ምንጭም መሆን ከመቻሉም በላይ አቶ አብዱልቃድር ለግብርና ሥራዎች ምን ያህል ፍቅርና ፍላጎት እንዳለውም ጭምር ያስተዋለበት አጋጣሚ ነበር፡፡ የመኖሪያ ግቢው በአትክልትና ፍራፍሬ ሙሉ በሙሉ ሲሸፈን ደግሞ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኘው ምክር አንድ የንብ ቀፎ ገዝቶ ወደ ንብ ማነብ ሥራ ገባ፡፡ አቶ አብዱልቃድር ለንብ ማነብ ሥራው አዲስ በመሆኑ ሥራውን በጀመረበት ወቅት በጣም ተቸግሮ እንደነበርና የሚጠበቀውን ያህል የማር ምርት እንዳላገኘም ይናገራል፡፡ ይህን ክፍተት ለመሙላት በንብ እርባታ ላይ የተፃፉ ፅሁፎችንና የሬድዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን መከታተል እንዲሁም ከባለሙያዎች ጋር መመካከር የዕለት ተዕለት ተግባሩ ሆነ፡፡ በሥራው ላይ ያለው ዕውቀት እየጨመረ ሲመጣም በቅድሚያ አስር ባህላዊ ቀጥሎም ወደ ዘመናዊ የሚያሻግሩ 15 ቀፎዎችን እና 2 ዘመናዊ ቀፎዎችን ገዝቶ የንብ ማነቡን ሥራ በሰፊው ተያያዘው፡፡ በጊዜ ሂደትም ዘመናዊ ቀፎዎችን መጠቀም ምርታማነትም ሆነ ጥራት ለመጨመር የሚያስችል መሆኑን በመረዳቱ በ50 ዘመናዊ እና በ27 የሽግግር (የባህላዊና ዘመናዊ ቀፎ ባህሪን አጣምረው የያዙ) ቀፎዎችን በመጠቀም በዓመት አስከ 100ኪ.ግ የሚደርስ ማር ማምረት ቻለ፡፡ ‹‹የሙያ ፍቅርና የቢዝነስ ክህሎት›› አንድ ላይ ሲጣመሩ ውጤታማ ያደርጋሉ የሚለው አቶ አብዱልቃድር ለንብ ማነብ ሥራ ያደረበትን ጥልቅ ፍቅር በስኬታማ ቢዝነስ ለመደገፍ የሚስችሉትን አማራጮች ዘወትር ከማማተር ወደኋላ ብሎ አያውቅም፡፡ ባካሄደው ጥልቅ ምልከታም ምንም እንኳን ድሬዳዋ ሞቃታማ የአየር ፀባይና በአካባቢው የሚበቅሉ እፅዋት ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ ቢሆንም በአካባቢው በቂ የንብ መንጋ የማግኘት ችግር መኖሩን ተገነዘበ፡፡ ንብ ማባዛትና ማከፋፈል አስመልክቶ በግል ጥረቱ ባገኘው ዕውቀት መነሻነት የንብ መንጋዎች እያባዛ ለግብርና ቢሮዎች፣ በመስኩ የሥራ ዕድል ለሚፈጠርላቸው ወጣቶችና የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ከ7ሺ እስከ 20ሺ ብር በሚያወጣ ዋጋ ከአንድ መቶ በላይ መንጋዎችን መሸጥ እንደቻለ ይናገራል፡፡ አቶ አብዱልቃድር በአሁኑ ጊዜ ከማር ምርትና ከንብ መንጋ ሽያጭ በተጨማሪ የማር እንጀራ በመጋገር ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ በሥራው ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ የአካባቢው ወጣቶች ስልጠናም ይሰጣል፡፡ ከንብ ማነብ ጋር በተያያዘ ያለውን ዕውቀትና ክህሎት ለማዳበር በየዕለቱ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ዘርፉን አስመልክተው የተዘጋጁ ፅሁፎችን እንደሚያነብ ይናገራል፡፡ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአውሮፓ ፈንድ የሚደገፍና በዘርፉ የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ስልጠናን በኦንላይን ተከታትሎ የምስክር ወረቀት ባለቤት መሆን የቻለ ሲሆን በ2025 በዴንማርክ፣ ኮፐንሃገን በሚካሄደው ‹‹ዓለም አቀፍ የንብ ማህበረሰብ ጉባኤ›› ላይ ተሳታፊ ለመሆንም ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ አማርኛ፣ ኦሮምኛ ሶማልኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረው አቶ አብዱልቃድር ‹‹የምስራቅ አፍሪካ የንብ ማህበረሰብ›› ለመፍጠር የዋትሳፕ ፕላትፎርምን በመጠቀም በሶማሊያ፣ በኬኒያ፣ በኢትዮጵያና ታንዛኒያ የሚገኙ 350 በመስኩ የተሰማሩ ሶማልኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በግሉ ማሰባሰብ እንደቻለ ይናገራል፡፡ በአማራና ትግራይ ክልል ከተቋቋሙ መሰል ፎረሞች ጋር የፈጠረው ግንኙነትም አዳዲስ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም በር ከፍቶለታል፡፡ አቶ አብዱልቃድር የማር ምርት በምስራቅ አፍሪካ ገበያ ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው መሆኑን በመረዳቱም በሥፋት ለማምረት የሚያስችል የመሬት ጥያቄ ለድሬዳዋ አስተዳደር አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ የመሬት ጥያቄው ምላሽ ሲገኝም በዓመት 40ሺ ኪሎ ግራም ማር አምርቶ ወደ ውጭ የመላክ ዕቅድን ይዟል፡፡ ከራሱ አልፎ የአካባቢውን ማህበረሰብም ጭምር ተጠቃሚ ለማድረግ ለአርሶ አደሮች ተገቢውን ሥልጠና በመስጠት፣ ጥራት ያለውን የንብ መንጋ በማቅረብና የምርት ሂደታቸውን በመቆጣጠር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ዕቅድ መንደፉንም ይናገራል ፡፡
amAM
Scroll to Top