Mols.gov.et

‹‹ብሩህ እናት›› የፈጠራ ሃሳብ ውድድርን በጋራ ለማዘጋጀት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

የካቲት 1, 2024
‹‹ብሩህ እናት›› የፈጠራ ሃሳብ ውድድርን በጋራ ለማዘጋጀት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ‹‹ብሩህ እናት›› በሚል ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያካሄደውንና ሴቶች ብቻ ተሳታፊ የሚሆኑበት የፈጠራ ሃሳብ ውድድርን ከእናት ባንክ ጋር በጋራ ለማዘጋጀት የሚያስችል የሥምምነት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት አካሄደ፡፡ የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ የሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ብሩህ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር አዳዲስና ችግር ፈቺ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የማወዳደር፣ የማብቃትና የመሸለም ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ይህ ውድድር በየዓመቱ በተለያየ ሥያሜና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በማተኮር ሲካሄድ መቆየቱን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ‹‹ብሩህ እናት›› በሚል ሥያሜ ሴቶች ብቻ በማሳተፍ እንደሚያካሄድ ጠቁመዋል፡፡ በተለያየ ደረጃ በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ሴቶችን በሚጠበቀው ልክ ከማካተት አንፃር በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ክፍተት እንደሚስተዋል ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጠቁመው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ክፍተቱን ለማጥበብ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እናት ባንክን ከመሳሰሉ የፋይናንስ ተቋማትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከእናት ባንክ ጋር የተፈራረመው የጋራ መግባቢያ ስምምነት ‹‹ብሩህ እናት›› የፈጠራ ሃሳብ ውድድርን በጋራ ከማዘጋጀት ባለፈ በአገር ውስጥ ምቹ የሥራ ዕድልን ለሴቶች ለማመቻቸት የሚያስችሉና እና ወደ ውጭ አገራት ለሥራ የሚጓዙ ሴቶች ወደ አገራቸው ሲመለሡ በተለያየ የሥራ መስክ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ ፓኬጆችንም አካቶ ይዟል፡፡
amAM
Scroll to Top