Mols.gov.et

ሚኒስቴሩ በውስጥ አቅም ካለማቸው 18 ማይክሮ ሰርቪሶች መካከል ሁለቱን ይፋ በማድረግ ወደ ሥራ አስገባ

ጥቅምት 5, 2024
ሚኒስቴሩ በውስጥ አቅም ካለማቸው 18 ማይክሮ ሰርቪሶች መካከል ሁለቱን ይፋ በማድረግ ወደ ሥራ አስገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በውስጥ አቅም አልምቶ ወደ ሥራ ያስገባው ‹‹የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት›› አካል የሆኑ ሁለት አዳዲስ ማይክሮ ሰርቪሶችን ይፋ ያደረገበት የማብሰሪያ ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የበለፀጉትን ስርዓቶች መርቀው ወደ ሥራ አስገብተዋል፡፡ ወደ ሥራ ከገቡት አገልግሎቶች መካከል ‹‹ኢ- ለርኒንግ›› አንዱ ሲሆን ዜጎች የትኛውም ቦታ ሆነው ብቃታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ትምህርትና ሥልጠና የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፡፡ ሌላውና ሁለተኛው አገልግሎት የሳይኮሜትሪክ ምዘና ለክህሎት ልማት የተሰኘ ሲሆን ስርዓቱ የሳይኮሜትሪክ ምዘናዎች በሃገራችን ባህል፣ ቋንቋ እና ይዘት ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ተደራሽ የሚሆኑበት ነው፡፡ በዚህ ስርዓት ዜጎች ውስጣቸው ያለውን ፍላጎትና ዝንባሌያቸውን በመለየት ትክክለኛ ተሰጥኦና መክሊታቸውን አውቀው ውጤታማ የሚሆኑበት ሥራ እና ስልጠና ላይ እንዲሰማሩ የሚያግዝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች የፋይናንስ አጠቃቀም ብቃታቸውን በመመዘን ያለምንም የብድር ማስያዣ የፋይናንስ ድጋፍን ለመስጠት አመኔታን የሚፈጥርና ፍትሃዊ የፋይናንስ ስርዓትን ከማስፈን አንፃርም ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በማብሠያ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ አስረድተዋል፡፡ በዕለቱ በይፋ ወደ ሥራ የገቡትን ሁለት ማይክሮ ሰርቪሶች ጨምሮ የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት 23 የሚደርሱ ሥርዓቶችን ማልማት እንደቻለና ከእነዚህም ውስጥ 18 ያህሉ ወደ የማበልጸግ ስራቸው የተጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
amAM
Scroll to Top