የአሠሪና ሠራተኛ ማህበራት- ለምርታማነት
ታህሳስ 25, 2024
የአሠሪና ሠራተኛ ማህበራት- ለምርታማነት
ሠራተኞች የሥራ ሁኔታቸውን ለማሻሻል፣ መብትና ጥቅማቸዉን ለማስከበርና የኢንዱስትሪ ሠላምን ለማረጋገጥ በማህበር የመደራጀት፣ የመመካከርና የመደራደር መብት እንዳላቸው በአለም ሥራ ድርጅት ድንጋጌ 87/1948 እና 98/1949 በግልፅ ሰፍሯል፡፡
የሀገራችን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 113/1 ሠራተኞችና አሠሪዎች እንደአግባቡ የሠራተኞች ወይም የአሠሪዎች ማህበር ለማቋቋምና ለማደራጀት፣ የማህበር አባል ለመሆን እና በማህበር ለመሳተፍ መብት እንዳላቸው ይገልፃል፡፡
በሌላ በኩል አንቀጽ 114/3 የሠራተኛ ማህበራት በአንድ ላይ በመሆን የሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ሊመሰርቱ ይችላሉ በማለት ደንግጓል፡፡ በተጨማሪም የኢፌዲሪ አስፈጻሚ አካላት ተግባርና ስልጣን ለመወሰን የወጣዉ በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 25/ ሰ/ሸ/ተ ሥር አሠሪዎችና ሠራተኞች በማህበር የመደራጀትና የኀብረት ድርድር የማድረግ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ያበረታታል፣ ይደግፋል፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደራጁትን የሠራተኛና የአሠሪ ማህበራት ይመዘግባል፣
ማህበራትን ማጠናከር የሚያስገኘው ጠቀሜታ
• አሠሪና ሠራተኞች በጋራ ጥቅሞቻቸዉ ላይ በመመካከርና በመደራደር ስምምምነት ለመድረስ ይረዳል፣
• አሠሪና ሠራተኞች የሥራ ቦታቸዉን ምቹ ለማድረግ ይረዳል፣
• ዲሞክራሲያዊ ባህልን ብሎም መልካም አስተዳደርን በማዳበር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዲመዘገብ አስተዋፆ ያደርጋል፤
• በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሰመረ ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙት እንዲኖር እና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ሠራተኞች ግዴታቸዉን በአግባቡ እንዲወጡ ይረዳል፤
• ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ፣በሚገኘዉ ትርፍ የሠራተኛዉ ኑሮ እንዲሻሻል፣ እንቨስትመንት እንዲስፋፋና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያስችላል፤
• አሰሪና ሠራተኞችን ጥቅምና መብት በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ሁለትዮሽና በሶስትዮሽ ማህበራዊ ምክከር ለማድረግ ያስችላል፤
• የሠራተኞች የሥራ ዋስትና እንዲረጋገጥ የደርጋል፡፡
የሠራተኞች በማህበር መደራጀት ምርትና ምርታማነትና ከማሳደግና የሠራተኞችንና የአሠሪዎችን መብት ከማረጋገጥ አንፃር ከላይ የተገለፁት ጠቀሜታዎች ያሉት በመሆኑ አሠሪዎች የሠራተኛ ማህበራትን በማቋቋምና በማጠናከር ረገድ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡