ክብርት ወ/ሮ ናቢሃ መሃመድ አብድላኪም በኤፌዴሪ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስቴር ዴኤታ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ወደዚህ ሃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት በሃላባ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ናቢሃ የሃላባ ዞን የከተማ ልማት፣ የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም የሴቶች ጉዳይ ፅ/ቤቶችን በሃላፊነት መርተዋል፡፡
በዞኑ የቤቶች ልማት ኤጀንሲ በባለሙያነት እንዲሁም በትምህርት ፅ/ቤት በሱፐርቫይዘርነት አገልግለዋል፡፡
‹ማስተማር የሁሉም ሙያዎች እናት ነው› እንደሚባለው ክብርት ወ/ሮ ናቢሃ የሥራን አለም ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀሉት በመምህርነት ነበር፡፡
የትምህርት ዝግጅታቸውን በተመለከተ በቅድሚያ ከሃዋሳ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ማስተማር በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በመቀጠልም የመጀመሪ ዲግሪያቸውን ከአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በቢዝነስ አስተዳደር እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በከተማ አስተዳደር አግኝተዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ናቢሃ መሃመድ የነፃነትና እኩልነት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሲሆኑ የፓርቲው የመንግስትና የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ካውንስል ሰብሳቢ በመሆንም በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡