Mols.gov.et

ድህነትን ለማሸነፍ ብሎም የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን እውን ለማድረግ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ አበርክቶ ጉልህ መሆኑ ተገለፀ።

ሚያዝያ 25, 2025
ድህነትን ለማሸነፍ ብሎም የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን እውን ለማድረግ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ አበርክቶ ጉልህ መሆኑ ተገለፀ። “ብሩህ አዕምሮዎች፣ በክህሎት የበለፀጉ እጆች” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የክህሎት፣የተግባራዊ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ውድድር፣ ሲምፖዚየምና አውደ ርዕይ በዱራሜ ከተማ ተካሄዷል፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በወቅቱ እንዳሉት ድህነትን ለማሸነፍና የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን እውን ለማድረግ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ አበርክቶ ጉልህ ነው፡፡ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በሁሉም ዘርፍ የላቀ እመርታ ለማስመዝገብ በእውቀት የበቃ የሰው ኃይልን ማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበርክትም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ በእውቀና ክህሎት የበለጸጉ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የኢፌዴሪ ቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ (ዶ/ር) በተቋማቱ የሚሰጡ ስልጠናዎች ጥራት ያላቸውና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ተቋማቱ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚረዱ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ የአካባቢን ፀጋ መሰረት በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በራሱ የስራ እድል መፍጠር የሚችል በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እሴት የሚጨምሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ መድረኩ በክልሉ በሚገኙ የቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በእውቀትና ክህሎት የበለጸጉ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ ናቸው፡፡ በክልሉ የሚገኙ 38 የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት የሚሰጡት የክህሎት ስልጠናዎች በጥራት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም የአካባቢን ፀጋ መሰረት ያደረጉና የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት ለማህበረሰቡ የማሸጋገር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በመርሐ ግብሩም የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ኃላፊዎችና የፈጠራ ባለቤቶች መገኘታቸውን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
amAM
Scroll to Top