የዘርፋችን የወቅቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የበቃ የሰው ሀይል ለኢኮኖሚው ከማቅረብ ባሻገር የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ማቅረብ ነው፡፡ ክቡር ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ
መስከረም 8, 2025

የዘርፋችን የወቅቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የበቃ የሰው ሀይል ለኢኮኖሚው ከማቅረብ ባሻገር የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ማቅረብ ነው፡፡
ክቡር ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር)
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች ሲሰጥ የቆየው ክፍተትን መሰረት ያደረገ የአሰልጣኝ ስልጠና መድረክ ተጠናቋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጠዘርፉ የወቅቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የበቃ የሰው ሀይል ለኢኮኖሚው ከማቅረብ ባሻገር የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ማቅረብ ነው ብለዋል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓቱን ከፍ የሚያደርጉ የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው ተግባራዊ ሲደረጉ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ለቴክኒክና ሙያ ተቋማት የድጅታል መሰረተ ልማት ማሟላት፣ ከብክነት የፀዳ የሀብት አጠቃቀም ተግባራዊ ማድረግ እና ወደ ብዝሃ ምርት የሚገቡ ውጤታማ ቴክኖሎጂዎች እና አጫጭር ስልጠናዎች ላይ አተኩሮ መስራት ላይ የሚጨበጥ ውጤት መመዝገቧል፤ በቀጣይም በልዩ ትኩረት ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የትምህርት የብቃት ማዕቀፍ በህግ መልክ እንዲጸድቅ በማድረግም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓቱ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ 8 ወይም እስከ ፒኤችዲ እንዲያድግ በማድረግ የአሰልጣኞች ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡
ለረዥም ጊዜ የቆየው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲና እስትራቴጂ ቀደም ሲል ያልነበሩ አዳዲስና ዘመኑን የዋጁ ጉዳዮች የተካተቱበት እና የነበሩ ነገር ግን መብራራት የሚገባቸው ጉዳዮችን በደንብ የተብራሩበት ሆኖ እየተዘጋጀ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ትኩረት ተነፍጎት የቆየው በልምድ የተገኘ ክህሎት የስልጠና ስርዓቱ አካል በማድረግ በርካታ ዜጎች ወደ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓት እንዲገቡ አስችሏል ብለዋል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የስልጠና ጥራት ለማረጋገጥ ከተቀረጹ ስትራቴጂዎች አንዱ የአሰልጣኞች ልማት ፕሮግራም በመሆኑ አሰልጣኞች ለማብቃት ተከታታይነት ያላቸው ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ባለፈው አመትም ከ25ሺህ በላይ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች በተደራጀ አግባብ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው በዚህ ዓመት ከአምናው ልምድ በመውሰድ በምዘና በተለዩ ክፍተቶች ላይ መሰረት በማድረግ 2500 ለሚሆኑ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በአሰልጣኝ ልማት ፕሮግራም ላይ በትኩረት መስራት አሰልጣኞች በዘርፉ የተቀረጹ ፖሊሲና እስትራቴጂ፣ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ ዘርፉ እንደ ሀገር የተጣሉበትን ሀገራዊ ተልዕኮዎች በብቃት ለመወጣት ተጨማሪ አቅም ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡
