የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ተገመገመ
ጥቅምት 12, 2026
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ተገመገመ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ፣ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በሩብ ዓመቱ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የታቀዱ የአጫጭር ስልጠናዎች በትኩረት የተከናወኑ ሲሆን፡ ዜጎችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ብቁ የሚደርጉ አጫጭር ስልጠናዎች በስፋት መሰጠቱ ተገልጿል፡፡
በ2019 የትምህርት ዓመት የመደበኛና አጫጭር ሰልጣኞች መቀበያ የመቁረጫ ነጥብ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁ የተገለፀ ሲሆን ለስልጠና ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ማሽነሪዎች በፌደራል እና በክልል በሰለጠኑ መሪ አሰልጣኞች አማካኝነት ተጠግነው ሙሉ በሙሉ ለስልጠና ዝግጁ መሆናቸውም ተነስቷል፡፡
አሰልጣኞች በሥነ-ምግባር፣ በዜግነት ኃላፊነት ፣ በሰውኛ ክህሎቶች (Human edge skills) እና በኢንተርፕረነርሽፕ ትምህርት ላይ በሶስት ማዕከላት የመጀመሪያ ዙር ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ሲሆን ከአጠቃላይ የተቋም አሰልጣኞች ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና መሰጠቱንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በሩብ ዓመቱ በካይዘን እና አካባቢ ጥበቃ (Green TVET) ዙሪያ ከGIZ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለተለያዩ ክልሎች መሪ አሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አመራሮች ሜሪትን መሰረት ያደረገ ምደባ 99% የተከናወነ ሲሆን፣ የሴት አመራሮችን ድርሻ 20% ለማሳደግ ከተያዘው ዕቅድ 19% ማድረስ ተችሏል።
ለ100 አመራሮች የተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ ለ250 አመራሮች በመስጠት የ100% አፈፃፀም ተመዝግቧል።
የምዘና አፈፃፀም ውጤትን በተመለከተ በመደበኛ መርሃግብር ከተመዘኑ ሰልጣኖች መካከል 40% ፣በገበያ-ተኮር አጫጭር ስልጠና 88% እንዲሁም ቀድሞ የተገኘ ብቃት ምዘና (RPL) ከተመዘኑ ግለሰቦች መካከል 64% ብቃታቸው መረጋገጡ ተብራርቷል፡፡
በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ተቋማዊ አውቶሜሽን ሥራዎች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ መግባት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
ISO 17024 (የፐርሶናል ሰርቲፊኬሽን ስታንዳርድ) ደረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን በውጤታማነት ማጠናቀቅና እንዲሁም የስልጠና ስታንዳርድ እና የስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ሰነዶችን (አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ) የማዘጋጀት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸውም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡


