የሰው ልጅን የፈጠራ ችሎታ ከቴክኖሎጂ ጋር ማጣመር
የካቲት 19, 2026
የሰው ልጅን የፈጠራ ችሎታ ከቴክኖሎጂ ጋር ማጣመር
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ሳምንታዊ የጥናትና ምርምር ሴሚናር ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘ በአራተኛው (4.0) እና በአምስተኛው(5.0) የኢንዱስትሪ አብዮቶች፣ በኢንዱስትሪ ሽግግርና በምዘና ሥርዓት ውጤታማነት ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ሪፖርት እና ዕቅድ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመድረኩ ላይ የቀረበው የመጀመሪያው የጥናት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ዓለም አቀፉ የኢንዱስትሪ አብዮት ከዲጂታላይዜሽን እና ከአውቶሜሽን ባለፈ የሰውን ልጅ የፈጠራ ችሎታ ከማሽኖች ጥምረት ጋር ወደሚያገናኘው አዲሱ ኢንዱስትሪ አብዮት 5.0 እየተሸጋገረ ይገኛል። ይህ ለውጥ በተለይም በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች አዳዲስና ዘመናዊ የክህሎት ዓይነቶችን እንዲላበሱ የሚያስገድድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ማሽኖች ያለ ሰው ንክኪ እንዲግባቡና ራሳቸውን ችለው ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያደርግ ሲሆን አምስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ደ ደግሞ ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ የመፍጠር አቅም እንዲያግዝ እንጂ እንዲተካው የማይፈለግበት ሥርዓት ነው።
ይህ አዲሱ አብዮት ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና ኢንዱስትሪዎች በችግር ጊዜ በቀላሉ የማይወድቁበትን ጥንካሬ መገንባት ላይ ትኩረት ያደርጋል።
ሆኖም አሁን ያለው የሀገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ-ትምህርት አሁንም በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ቴክኖሎጂዎች ላይ ገና እየተንደረደረ መሆኑና በዲጂታል ፋሽን ንድፍ፣ በስማርት ማምረቻ እና በዘላቂነት ረገድ ሰፊ የክህሎት ክፍተት መኖሩ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ሰልጣኞች ማሽኖችን ከማንቀሳቀስ ባለፈ የፈጠራ አስተሳሰብ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ጠንቅቀው ማወቅ እንዳለባቸው ጥናቱ አሳይቷል።
ለዚህም እንደ መፍትሄ የቀረቡት ምክረ-ሀሳቦች የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻል፣ ቴክኖሎጂ በየጊዜው የሚቀየር በመሆኑ የዕድሜ ልክ ትምህርት ግንዛቤን ማስረጽ፣ የመንግስትና የኢንዱስትሪ ትብብርን ማጠናከር፣ እንዲሁም ማሽኖች ሊተኳቸው የማይችሏቸውን የሰው ልጅ ልዩ ባህሪያት (Soft Skills) ማዳበር የሚሉ ናቸው። ይህም ሰልጣኞችን ከቀጣሪነት ባለፈ የቴክኖሎጂ መሪ እና ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል።
በተጨማሪም በሴሚናሩ ማጠናቀቂያ ላይ በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የምዘና ልምዶች እና ምሩቃን ብቃት ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ የሚያሳይ የጥናት ዕቅድ (Proposal) ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። ይህ የጥናት ዕቅድ ወደፊት በዘርፉ ላይ የሚታዩ የአፈጻጸም እና የጥራት ችግሮችን ለመፍታት እንደ ዋነኛ ግብዓት ያገለግላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል፡፡







