ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ
በሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና ያላቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና የመንግስት ተቋማት የተሳተፉበት ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ውይይት ተካሄዷል፡፡
የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና የመንግስት ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የሥራ ዕድል ፈጠራ ማነቆዎችን በጋራ መፍታትና በየተቋማቱ የሚገኙ የሥራ ዕድል ጸጋዎች አሟጦ በመጠቀም ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የልማት ድርጅቶች እና ክልሎች የሥራ ዕድል ፈጠራ እቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በኢንተርፕራይዝ ምስረታ እና በቅጥር የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች እንዲሁም ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት ውጤታማ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ተቋማት ተሞክሮአቸውን አጋርተዋል፡፡
ዜጎች በሥራ ዕድል ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይ ለአንድ አካል የሚተው ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ በመድረኩ አጽንኦት ተሰጥቶታል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሀገራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራውን ሂደት የማስተባበር፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም መሆኑን ይታወቃል፡፡