Mols.gov.et

ከስልጠና በላይ…

ህዳር 10, 2025
ከስልጠና በላይ… ስልጠና አጠናቃቂዎቹን ከሥራ ጋር በማስተሣሰር አብነት እየሆነ ያለው ኮሌጅ በኮሪያ መንግስት ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ኮይካ) እና በኤልጂ ኤሌክትሮኒክስ ድጋፍ የተቋቋመ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋም ነው፣ ኤል ጂ ኮይካ ሆፕ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፡፡ የሥራ ገበያውን ፍላጎትንእና የኤልጂን ኩባንያ ቁልፍ የሙያ ክህሎትችን፣ ብቃቶችንና ቴክኖሎጂዎችን መሰረት በማድረግ በኤሌክትሮኒክስ፣ በአይሲቲና ተዛማች መስኮች ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት ይታወቃል። የኮሌጁ ዲን አቶ ታሪኩ ገብረ መድህን እንደሚገልፁት ስልጠናው በኤል ጂ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ተቋም የጥራት ስታንዳርድ መሰረት የሚሰጥ ነው። ይህም ሰልጣኞችን በሥራ ገበያው ላይ የላቀ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ኮሌጁ ከሥልጠና ባለፈ ለስልጠና አጠናቃቂዎቹ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ ዕድል በማመቻቸት ከሥራ ጋር እንዲተሣሰሩ ያደርጋል። በዚሁ መሰረት በዱባይ ፣ በኬኒያ፣ በጅቡቲ እና በሞሪሺየስ በሚገኙ የኤል ጂ ኤሌክትሮኒክስ ቅርንጫፎች ውስጥ ብቁና ተወዳዳሪ ለሆኑ ባኮሌጁ ምሩቃን የሥራ ዕድል ማመቻቸት መቻሉንም አቶ ታሪኩ ይገልፃሉ። ኮሌጁ ለስልጠና አጠናቃቂዎቹ የራሳቸውን ቢዝነስ አቋቁመው ወደ ሥራ እንዲገቡም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ድጋፉ በኤሌክትሮኒክስ ጥገና ላይ መሠማራት ለሚፈልጉ ለሥራ መጀመሪያ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ማሟላትን ያካትታል፡፡ በዚሁ መሰረት በአዲስ አባባ ብቻ 123 ቢዝነሶች በኮሌጁ ምሩቃን ተከፍተው እየሠሩ እንደሚገኙ የኮሌጁ ዲን ጨምረው አሳውቀዋል፡፡ ተቋማት የኮሌጁን ሰልጣኖች ቢቀጥሩ የሚያገኙትን ጠቀሜታ የሚያመለክት መረጃ የያዘ መጽሐፍ(employment book) በኮሌጁ በየዓመቱ ተዘጋጅቶ ለተለያዩ ቀጣሪ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ይሰራጫል፡፡ ይህም ቀጣሪ ተቋማት የሚፈልጉትን የሰው ኃይል በቀላሉ ለማግኘት እንደሚረዳቸው የሚናገሩት አቶ ታሪኩ በዚህ መልኩ ለኮሌጁ ምሩቃን የሥራ ዕድል አማራጮችን የማስፋት ሥራ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ በየዓመቱ የሚዘጋጀው ሥራ አውደ ርዕይ(job fair) የኮሌጁ ምሩቃን አቅም ለቀጣሪ ተቋማት በማስተዋወቅ የሥራ ዕድል የሚመቻችበት ሌላው አማራጭ እንደሆነም አቶ ታሪኩ ይናገራሉ፡፡ የሥራ ገበያ መዳረሻዎችንም በማስፋት በኮሪያና በሌሎች ሀገራት ላይ ሰልጣኞችን በብቃትና በጥራት አሰልጥኖ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡ የማህበራዊ ሃለፊነትን ከመወጣት አንጻርም ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠራና በተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ለሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችና ማሽኖች ነፃ የጥገና አገልግሎት እንደሚሰጥ የኮሌጁ ዲን አመላክተዋል። ሰልጣኞች የቀሰሙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነ በኮሌጁ የጥናትና ምርምር፣ የማህረሰብ አገልግሎት እና ኢንኩቤሽን ክፍል ሃላፊ አቶ ወንድምአገኝ አለምአየሁ ይናገራሉ። ኮሌጁ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጠራን እንዲሁም የቴክኖሎጂ ንግድ ሐሳቦችን ማፍለቅና አዲስ የተቋቋሙ ሥራዎችን (Start-up) የመደገፍ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ የኢንኩቤሽን ማዕከልንም አቋቁሟል ብለዋል። በኮምፒውተርና የሞባይል ስልክ ጥገና፣ በግራፊክስና ኤዲቲንግ፣ በፕሮግራሚንግ፣ በፍሪጅ፣ በፎቶ ኮፒ ማሽን፣ በኤይር ኮንዲሽነር ማሽንና በቴሌቪዥን ጥገና ዘርፎች ላይ አጫጭር ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አቶ ወንድምአገኝ ተናግረዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት እርዳታና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወጣቶች በኤሌክትሮኒክስ ኮሙኒኬሽን፣በመልቲሚዲያ፣ የአይሲቲ ሀርድዌር እና ኔትወርኪንግ ፕሮግራሞችን ነፃ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
amAM
Scroll to Top