ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት…
ጥር 1, 2026
ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ተጉዘው እንዲሠሩ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
ባለፉት አምስት ወራት በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ1 ሺህ 300 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ለየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅና ለመከታተል መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገው ከፍተኛ ክትትል ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 1 ሺህ 300፣ እንዲሁም በሳውዲ ዓረቢያ የነበሩ 26 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ገልጸዋል።
ዜጎቹን ከነበሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ፤ አሁንም በደላሎች ያልተጨበጠ መረጃ የሚታለሉ ዜጎች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ እየሄዱ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። በመሆኑም ዜጎች ለሕይወት አስጊ ከሆኑ ሕገ-ወጥ ጉዞዎች ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሄደው እንዲሠሩ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። በተለይም በአረብ ሀገራት በሚገኙ ቆንስላዎች ዜጎችን የሚከታተሉ ዲፕሎማቶች ተመድበው የቅርብ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
ከአሠሪዎቻቸው ጋር ችግር ለሚገጥማቸው ዜጎች የሕግ ድጋፍና ክትትል የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
ዘገባው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ነው

