ባለፉት ሰባት ወራት ከ447 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል
መጋቢት 3, 2026
ባለፉት ሰባት ወራት ከ447 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል
የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ስትሪንግ ኮሚቴ ዕቅድ አፈፃፀሙን ክቡር አምባሳደር አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ገምግሟል፡፡
በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ከ447 ሺህ በላይ ዜጎችን ጥራት ያለው የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ ላይ እንደተመለከተው፣ የተመዘገበው ስኬት የሰው ኃይል ዝግጅትን፣ የሥራ ገበያ ፍላጎትንና ለሥራው ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርን ማዕከል ባደረገ የጋራ ዕቅድ ሁሉም ባለድርሻና አስፈፃሚ አካላት ተሰናስለው በመስራታቸው መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ የተቀናጀ አሠራር የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ባለፉት ሰባት ወራት በተተከናወኑ ሥራዎች የተገኘው ውጤት፤ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሻሻል የታየበት መሆኑ ተመላክቷል።
በቀጣይም በሰው ኃይል ዝግጅት ረገድ የግል ዘርፉና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው ድርጅቶች በስፋት እንዲሳተፉ ማበረታታት እንደሚገባ ተመላክቷል።
ይህም የዜጎችን ተወዳዳሪነትና የሥራ ጥራት ይበልጥ ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑና የተጀመሩ የቅንጅት ሥራዎችን በላቀ ትጋት ማጠናከር እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡








