Mols.gov.et

በፈጠራ ሥራው ለብዙኃን ብርሃን የፈነጠቀው ወጣት

ታህሳስ 21, 2025
በፈጠራ ሥራው ለብዙኃን ብርሃን የፈነጠቀው ወጣት ብዙዎች ችግርን ሲያማርሩ ጥቂቶች ግን ወደ ዕድል ይቀይሩታል። ወጣት ፌደሳ ሹማ ከእነዚህ ጥቂት ባለ ራዕይ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ በኢትዮጵያ የተሰራ በሚል ስም ድምጽና ጭስ አልባ ዘመናዊ ጄነሬተሮችን የሚያመርተው “ፌዶ ፓወር ሶሉሽን” (Fedo Power Solution) ባለቤት ነው፡፡ የወጣቱ የጥረትና የፈጠራ ውጤት ዘመናዊና ለአካባቢ ተስማሚ ጄኔሬተር ሲሆን፤ ወጣት ፌዴሳ ምርቱን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ሕልም ሰንቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወጣቶች በሰመር ካምፕ የሰሯቸውን የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በተመለከቱበት ወቅት፤ ሀገር የምትሻገረው ከትንሽ ተነስተው ወደ ትልቅ ኩባንያዎች በሚያድጉ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ የፈጠራ ስራዎቹ ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት እንደሚጥሉ ጠቅሰው፤ የተመለከቱት ጄኔሬተር አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደረጎ ተጨማሪ ነዳጅ ሳይጠቀም ለበርካታ ሰዎች ብርሃን መስጠት የሚያስችል ድንቅ የፈጠራ ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ የፈጠራ ስራዎች ኢትዮጵያውያንን ወደ ተሻለ አኗኗር የሚያሸጋግሩ ናቸው ነው ያሉት፡፡ የፌዶ ፓወር ሶሉሽን መስራች ወጣት ፌደሳ ሹማ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው፤ የፈጠራ ስራውን የጀመረው በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በስራው ላይ በፈጠረበት ተግዳሮት የተነሳ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ለስራው ይጠቀምበት የነበረው ጄኔሬተር ነዳጅ የሚጨርስ፣ ድምፁ የሚረብሽና ጭስ የሚያወጣ መሆኑ ለወጣቱ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖበት እንደነበርም ያስታውሳል፡፡ ይህንኑ ችግር ለማቃለል መፍትሄ መፈለግ የጀመረው ወጣት ፌደሳ በ2014 ዓ.ም የራሱን ጄኔሬተር በመሥራት የፈጠራ ሕልሙን ዕውን ማድረጉን ተናግሯል፡፡ ወጣቱ በፈጠራ ሥራው ለመጀመሪያ ጊዜ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ውድድር አሸናፊ በመሆን የፈጠራ አቅሙን መረዳት እንደቻለ ያስታውሳል፡፡ ከዛም በዞን፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የተደረጉ የፈጠራ ውድድሮችን በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የ260 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ማግኘቱ ለስራው ማደግ የራሱ ሚና እንደነበረው ጠቅሷል፡፡ ይህ ሽልማት ለትልቅ ሕልሙ መነሻ እንደሆነው የሚናገረው ወጣት ፌደሳ፤ መጀመሪያ በ300 ኪሎ ዋት የጀመረው የፈጠራ ሥራ ዛሬ ወደ 600 እና አንድ ነጥብ አምስት ሜጋ ዋት መሸጋገሩንም ተናግሯል፡፡ ፌዶ ፓወር ሶሉሽን የሚያመርታቸው ጄኔሬተሮች ድምፅና ጭስ አልባ መሆናቸው ለአካባቢ ጥበቃና ለጤና ተስማሚ አድርጓቸዋል። ፌዶ ፓወር ሶሉሽን የሥራና ክህሎት፣ የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት በክህሎት ኢትዮጵያ ካፈሯቸው የሥራና የፈጠራ ሥራ ባለሙያውች አንዱ ነው። ዘገባው የኢዜአ ነው
amAM
Scroll to Top