በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት
መጋቢት 12, 2026
በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ የአሰራር ምኅዳር መፈጠሩ ተገለፀ
በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ የአሰራር ምኅዳር መፈጠሩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ።
ቢሮው በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከዛሬ መጋቢት 2/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የሥራ አውደ ርዕይ ከፍቷል።
“የግል ዘርፍ ተሳትፎ፤ የብቁ ወጣቶች ማንሰራራት ለገሀር ልዕልና” በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው የሥራ አውደ ርዕይ ላይ 6ሺህ የሚሆኑ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችና ሴቶች ቀጥተኛ ሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል እንደሚመቻች ተገልጿል።
የሥራ አውደ ርዕዩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መርቀው ከፍተውታል።
በዚሁ ጊዜ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት መሰረት እየጣለ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ሥራ ፈላጊዎችን በማደራጀት ከሥራ ቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍም ሥራ ፈላጊዎችና ቀጣሪዎችን የሚያገናኝ ምቹ ምህዳር መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ የ24/7 የሥራ ባህልም የከተማዋን ልማትና ዕድገት በማስቀጠል የበርካታ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የቢሮ ምክትልና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አስፋው ለገሰ በበኩላቸው፤ በሰባት ወራት ውስጥ ከ280ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሥራ አውደ ርዕዩ የሚሳተፉ ከ200 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚያስፈልጋቸውን የሰለጠነ የሰው ሃይል በመመልመል በርካታ ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ዘገባው የኢዜአ ነወ።




