Mols.gov.et

በቆዳ እና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ብቃት ያለው ሙያዊ ሥልጠና …

ነሐሴ 6, 2026
በቆዳ እና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ብቃት ያለው ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደረገ የኦሮሚያ ሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ከጣሊያን ማርቼ ክልላዊ መንግሥት(Marche region) ጋር በመሆን በቆዳ እና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ብቃት ያለው ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቅንጅት መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል። የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ኤባ ገርባ እንደገለጹት፤ ይህ ውይይት በቆዳ እና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ጥራትና ብቃት ያለው ሥልጠና ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ፣ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጆችን የማስፈጸም አቅም ማጠናከር፣ የአገራችንን የማምረት አቅም ማሳደግ እንዲሁም የቆዳ እና የጫማ ምርት ዘርፍን የዘላቂ ሥራ ዕድል ምንጭ ለማድረግ የሚያስችል ትልቅ እርምጃ ነው። ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ለመፍጠር፣ የኢንተርፕራይዞቻችንን የመነሻ ገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ውይይቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ኢንጂነር ኤባ ተናግረዋል። የማርቼ ክልላዊ መንግሥት ተወካይ አቶ ናታሊኖ ባርቢዚ በበኩላቸው፤ ክልላዊ መንግሥታቸው በቆዳና በጫማ ምርት ዘርፍ የሙያ ሥልጠናን ለማጠናከር፣ የሰው ኃይል አቅምን ለማሳደግ እና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከሲቪኤም (CVM) ከሚባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እና ከዩኒዶ (UNIDO) ጋር በመሆን ከኦሮሚያ ሥራ ዕድል ፈጠራና ሙያ ቢሮ ጋር ለመሥራት ማቀዱን ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወኑ ሥራዎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት ይህ ውይይት ወሳኝ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። ዘገባው የኦሮሚያ ሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ነው
amAM
Scroll to Top