Mols.gov.et

ስምንት መቶ ሺህ የገጠር ወጣቶች ተጠቃሚ…

ሚያዝያ 7, 2026
ስምንት መቶ ሺህ የገጠር ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርገው ራዕይ 2 (RAYEE II) ፕሮግራም ወደ ትግበራ ሊገባ ነው በኢትዮጵያ በገጠር ለሚገኙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግባራዊ የሚደረገው ራዕይ 2 (RAYEE II) ፕሮገራም የከፍተኛ አመራር የስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት ተካሄዷል፡፡ መንግስት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽንና ከኤስ ኤን ቪ(SNV) ጋር በመተባበር የሚተገብረው ይህ ፕሮግራም፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ 800 ሺህ ለሚሆኑ የገጠር ወጣቶች ጥራት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ነው። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታና የፕሮግራም አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በመክፈቻ ንግግራቸው ፣ ራዕይ 2 (RAYEE II) ፕሮግራም 90 በመቶ ተጠቃሚዎች ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው ከመደበኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ስር የሰደዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍና ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ የተነደፈ ነው ብለዋል። አክለውም ፕሮግራሙ ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ከሀገራዊ የልማት ግቦች ጋር ተሳስሮ ይፈጸማል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም የሀገርን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ተግባራዊ እየተደረገ ከሚገኘው የሌማት ቱሩፋት ( በዶሮ እርባታ፣ በወተትና በአትክልትና ፍራፍሬ) ዘርፎች ጋር በማስተሳሰር ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ የሚመሩት ይህ ፕሮግራም፣ በሰባት የሀገሪቱ ክልሎች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል። በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመውና በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚመራው ይህ ስትሪንግ ኮሚቴም በቀጣይነተ በአተገባበር ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየገመገመና እየፈታ ይሄዳል ተብሏል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ (Phase I) ከ278 ሺህ በላይ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር የቻለው ራዕይ (RAYEE)፣ አሁን በሁለተኛው ምዕራፍ በላቀ በጀትና ስትራቴጂ የኢትዮጵያን የገጠር ኢኮኖሚ ማነቃቃት እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡
amAM
Scroll to Top