ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን …
የካቲት 21, 2026
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ ነው – ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ 11ኛውን የሕብረት የስምምነት ተፈራርመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የአሠሪና ሠራተኛ መልካም ግንኙነት መኖሩ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻል የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዋነኛው መሣሪያ መሆኑንም አፅንዖት አንስተዋል።
በዕለቱ የተፈረመው የሕብረት ስምምነትም በአየር መንገዱ አመራርና በሠራተኛው መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥና ለተቋሙ ዘላቂ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አመላክተዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ ስምምነት በሚኒስቴሩ የታለመውን ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት የመገንባት ራዕይ በተግባር የሚያሳይ ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ የሕብረት ስምምነቱ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ቀጣይነት ያለው ስኬት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ገልፀዋል።
የሕብረት ስምምነቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዕድገት በማፋጠን የሠራተኞችን ጥቅም በዘላቂነት የሚያስከብር መሆኑንም አብራርተዋል።






