ማኅበረሰብ-አቀፍ የምርታማነት ውይይት ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዟችን የፈጠነ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
ታህሳስ 2, 2024
ማኅበረሰብ-አቀፍ የምርታማነት ውይይት ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዟችን የፈጠነ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በየደረጃው ለሚያካሂደው የማህበረሰብ-አቀፍ የምርታማነት ውይይት ለአዲስ አበባ አስተዳደር የአመቻችነት የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
በሥልጠና ማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት፣ ማኅበረሰብ-አቀፍ የምርታማነት ውይይት የሥራ ባህላችንን በማሳደግ፣ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም የማህበረሰባችንን እሴት የማከልና የመፍጠር አቅምን ለማውጣት ያለመ ነው፡፡
ይህም ዜጎች አካባቢያቸውን እና የልማት ፀጋዎቻቸውን እንዲያስተውሉ፣ በችሎታቸው እንዲተማመኑና የማድረግ አቅማቸውን ከማሳደግ ባሻገር የቤተሰብን፣ የግለሰብንና የማህበረሰብን ምርታማነት የምናሳድግበት የለውጥ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
ሂደቱ በየአካባው ያሉ ችግሮችን በመለየት ወደ መልካም አጋጣሚነት መቀየርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ መነሻነት እያንዳንዱ አካባቢ ፀጋውን መሰረት ያደረገ የራሱ መለያ የሚሆን ምርት ማውጣት እንደሚጠበቅበትም አመላክተዋል፡፡
ውይይቱ ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዟችን ያጠረና የፈጠነ፤ ፈጠራን ያከለና ያማከለ እንዲሆን እንደሚያደርግም ጨምረው ገልጽዋል፡፡
በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአዲስ አበባ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ተቀባ በበኩላቸው፤ ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የሥራ ባህልን ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል፡፡