ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያዘጋጀው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ…
ሰኔ 16, 2026
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚያዘጋጀው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ‹‹አካታችነት››ን ዋንኛ ምሰሶ ለማድረግ የሚያግዝ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ አካሄደ
በመድረኩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የስትራቴጂክ ዕቅድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢብርሂም ሰይፉ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚያስፈፅማቸው የክህሎት ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ዘርፎች ሴቶችን፣ ወጣቶችን አካል ጉዳተኞችንና ሌሎችን ተጋላጭ የህበረተሰብ ክፍሎች ላይ በይበልጥ የሚያተኩሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚቀረፁ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና መመሪያዎች ከዚሁ አንፃር የተቃኙ ከመሆናቸውም በላይ አዲሱ የዘርፉ እሳቤ ውስጥም አካታችነት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ዜጎችን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሚኒስቴር መ/ቤቱ እያዘጋጀ በሚገኘው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ውስጥ አካታችነት ዋንኛ ምሰሶ እንዲሆን ለማስቻል መድረኩ በሴቶችና አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚዘጋጁ ዕቅዶችና አፈፃፀሞች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሚገባ እንዲያካትቱ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ከአካቶ ትግበራ አንፃር ሰፊ የአመለካለካከትና የተግባር ክፍተት የሚስተዋል በመሆኑ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት መሰራት እንደሚኖርባቸውም በተወያዮች ተመላክቷል፡፡
አካታችነት ላይ ያተኮሩ ትክክለኛ መረጃዎችን ማሰባሰብና በተለያየ አጋጣሚ የሚገኙ መረጃዎችንም ዜጎችን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም በአፅንኦት ተነስቷል፡፡




