Mols.gov.et

«ሉሲ ገበያ»፦ ለኢንተርፕራይዞች ዲጂታል ሽግግር…

ሰኔ 6, 2026
«ሉሲ ገበያ»፦ ለኢንተርፕራይዞች ዲጂታል ሽግግር በዚህ እጅግ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዘመን የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ዲጂታል ስርዓቶች መጠቀም ምርጫ ሳይሆን የግድ ነው። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኤስ ኤን ቪ ሊዌ ፕሮግራምና ከአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ በመተባበር የኢንተርፕራይዞችን አቅም ለመገንባትና ምርቶቻቸውን ወደ «ሉሲ ዲጂታል ገበያ» ለማስገባት ለባለሙያዎች እየሰጠ ያለው ስልጠና ለዚህ ትልቅ ማረጋገጫ ነው። በዚህ የዲጂታል ሽግግር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን በገበያ ላይ ስኬታማ ለማድረግ ብራንዲንግ (Branding) እና ድጅታል ማስታወቂያ መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡ ጠንካራ ብራንድ የገነቡ ኢንተርፕራይዞች በደንበኞች ዘንድ ከፍተኛ እምነት ያተርፋሉ፤ ይህም ደንበኛው ያለ ምንም ማንገራገር ምርቱን እንዲሸምት ያደርጋቸዋል። የ«ሉሲ» የዲጂታል ገበያ ደግሞ ለኢንተርፕራይዞች ተራ የገበያ ቦታ ሳይሆን፣ ምርትና አገልግሎታቸውን በዘመናዊ መንገድ የሚያስተዋዉቁበትና ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ የሚያሳድጉበት ግዙፍ አማራጭ ነው፡፡ ይህ ፕላትፎርም ኢንተርፕራይዞች ከአካባቢያዊ ገበያ ወጥተው በመላው አገሪቱ አልፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርቶቻቸውን 24/7 (በየትኛውም ሰዓት) እንዲያስተዋውቁና እንዲሸጡ ዕድል ይፈጥራል። በሉሲ ፕላትፎርም ላይ የሚደረግ የብራንዲንግና ማስታወቂያ ሥራም ባህላዊ ማስታወቂያዎች (እንደ ቢልቦርድና ጋዜጣ) ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁትን በማስቀረት በቀጥታ ምርትና አገልግሎት ወደ ፈላጊው ደንበኛ ዘንድ የሚያደርስ መንገድ ነው። ከሁሉ በላይ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሳይቀሩ እንደ ትላልቅ ኩባንያዎች ሁሉ ምርታቸውን በሚያምር አቀራረብ (Professional Packaging & Digital Display) ለገበያ እንዲያቀርቡ ከማስቻል ባሻገር ከደንበኞቻቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር አስተያየቶችን በፍጥነት እንዲቀበሉና አገልግሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳል። በአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ስር ለሚገኙ የማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ባለሙያዎችን በኢ-ኮሜርስ፣ ሶሻል ሚዲያ ማርኬቲንግ እና በሉሲ ፕላትፎርም አጠቃቀም ላይ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ሲጠናቀቅ በአጭር ጊዜው በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንተርፕራይዞች ፕላትፎርሙን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
amAM
Scroll to Top