ለኢትዮጵያ ስታርትአፖች የዓለም አቀፍ ፋይናንስና የገበያ ዕድሎችን…
ሰኔ 12, 2026
ለኢትዮጵያ ስታርትአፖች የዓለም አቀፍ ፋይናንስና የገበያ ዕድሎችን የሚያሰፋ የአጋርነት ስምምነት
የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) በአገር ውስጥ ያሉ ስታርትአፖችን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን እንዲሁም በፈጠራ ላይ የተመሰረቱ የንግድ ተቋማትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ የአጋርነት ስምምነት በኖርዌይ መቀመጫነቱን ካደረገው ዩሮኖርዲክ ፈንዲንግ አሊያንስ (ENFA) ጋር ተፈራረመ።
ይህ አጋርነት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተገነባ ያለውን የሥራ ፈጠራና የስታርትአፕ ሥነ-ምህዳር ይበልጥ ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ለአገር ውስጥ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የገበያ በሮችን የሚከፍት መሆኑ ተገልጿል።
በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት የአገር ውስጥ ስታርትአፖች በቀላሉ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፎችን፣ የተቀላቀሉ ፋይናንሶችን (Blended Finance) እና የግል ኢንቨስትመንቶችን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ስታርትአፖች አቅማቸውን በማሳደግ ምርትና አገልግሎታቸውን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በተለይም ወደ አውሮፓ፣ ወደ ኖርዲክ አገራት፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ (MENA) ቀጠናዎች እንዲያስፋፉ ስትራቴጂካዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
ትብብሩ የሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ለመገንባት የሚያግዙ ልዩ ሥልጠናዎችንና የምክር (Coaching) አገልግሎቶችን የሚያካትት ሲሆን፣ አገር በቀል ፈጠራዎች በዓለም አቀፍ ጥምረቶች ውስጥ እንዲሳተፉ ዕድል ይፈጥራል።
በዚህ ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ ስታርትአፖች እና የስነ-ምህዳሩ አንቀሳቃሾች የዩሮኖርዲክ ፈንዲንግ አሊያንስ (ENFA) የሚያቀርባቸውን ዘመናዊ ዲጂታል አገልግሎቶች በይፋ ማግኘት የሚችሉ ይሆናል።
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የታገዙ የእርዳታና ፋይናንስ መፈለጊያ መሣሪያዎች፣ዓለም አቀፍ የኔትወርክና የትስስር መድረኮች፣የዓለም አቀፍ ፕሮጀክትና የገንዘብ መጠየቂያ ፕሮፖዛል ዝግጅት ድጋፎች፣ እንዲሁም
ከውጭ ኢንቨስተሮች ጋር በቀጥታ የሚያገናኙ የኢንቨስትመንት ትስስር (Matchmaking) ዕድሎች ከአገልግሎቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የተቋማቱ ተወካዮች በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ፈጠራና የቴክኖሎጂ አድማስን ለማስፋት ዓለም አቀፍ ትብብር ማድረጉ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይህ ተነሳሽነት የአገር ውስጥ ሥራ ፈጣሪዎች አስፈላጊውን ስትራቴጂካዊ ሀብትና ዕውቀት አግኝተው በዓለም መድረክ ላይ ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በቀጥታ ያግዛል።
ዩሮኖርዲክ ፈንዲንግ አሊያንስ (ENFA) ከ20 በላይ አገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፋይናንስ ድርጅቶችን፣ የባለሙያ ተቋማትን እና የፈጠራ አጋሮችን በአንድ ላይ ያቀፈ ትልቅ ዓለም አቀፍ ጥምረት ሲሆን፤ ይህ ስምምነት የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) በኢትዮጵያ ውስጥ ተንቀሳቃሽ፣ ዘመናዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገናኘ የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት የያዘውን አገራዊ ራዕይ የሚያፋጥን መሆኑ ታውቋል።
ዘገባው የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢኒስቲትዩት ነው;
