Mols.gov.et

የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ላይ የሚደረገው ምዝገባ ፋይዳው ሰፊ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ጥቅምት 21, 2024
የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ላይ የሚደረገው ምዝገባ ፋይዳው ሰፊ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የክልሎችን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀምን ግምገማን ቀጥሎ ዛሬ ከሰዓት በኋላ የአማራ ክልል የዘርፉ እቅድ አፈፃፀምን ተመልክቷል፡፡ በመድረኩ የክህሎት ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የማህበራዊ ጉዳይ እና የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ የሦስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በውይይቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ በዘርፉ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ ያለው የክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት የመፍጠር ሥራ የተለየ አካሄድን፣ የክትትልና ድጋፍ ሥራን የሚጠይቅ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ የተጀመሩ ስራዎችን ለማላቅ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ያመላከቱት ክብርት ሚኒስትር ለክህሎት ልማት፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለኢንተርፕራይዞች የተለያዩ ድጋፎችን ለማመቻቸት የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ላይ የሚደረገው ምዝገባ እንደ ሀገር ፋይዳው ሰፊ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
amAM
Scroll to Top