Mols.gov.et

አዋጁ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በአግባቡ በመምራት የዜጎችን ክብርና ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

ሐምሌ 2, 2025
አዋጁ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በአግባቡ በመምራት የዜጎችን ክብርና ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚደረጉ የሥራ ስምሪቶችን በአግባቡ በመምራት የዜጎችን ክብርና ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 41ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡ ዜጎች መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው እንዲጠበቅ የሚያደርግ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ብሔራዊ ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችል ነው። የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ለኢዜአ እንደገለጹት፥ አዋጁ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪትን በተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌዎችን አካትቷል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መሆኑን ጠቅሰው፥ አዋጁም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አኳያ የዜጎች ደህንነትና የሀገር ጥቅም መነሻ እና መዳረሻ እንዲሆኑ ማድረግን የተመለከተ ነው ብለዋል። አዋጁ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስቀረት በኩል ጉልህ ሚና እንዳለው በመጥቀስ፥ በውጭ ሀገራት መስራት የሚፈልጉ ዜጎችም ክብራቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ በህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ያደርጋል ነው ያሉት። አዋጁ በውጭ ሀገር ሥራ ላይ ሊሰማራ የሚችል ዜጋ የሥራ መደቡ የሚጠይቀውን የትምህርት ዝግጅት፣ ከፍተኛ የዘርፍ እውቀት፣ የሙያና የሥራ ልምድ እንዲኖራቸው የሚያስችል እንደሆነም ጠቅሰዋል። በሚቀጠሩበት የሥራ መስክ አግባብነት ካለው የምዘና ማዕከል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑንም ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት። ጠንካራ የሆነ የስልጠናና የማብቃት ስርዓት እንደ ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ዜጎች በራስ መተማመናቸውና የመደራደር አቅማቸው እንዲያድግ በማድረግ ረገድም አዋጁ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። አዋጁ የዘርፉ ተዋንያን ጠንካራ አደረጃጀትና የአሰራር ስርዓት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡
amAM
Scroll to Top