በከተማው ለወጣቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ
ሚያዝያ 16, 2025

በከተማው ለወጣቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ
የአዲስ አበባ የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የሁለተኛው ዙር የሌማት ትሩፋት የንቅናቄ ስራዎች አፈፃፀም ተገምግሟል።
በመድረኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የተከናወኑ አበይት ተግባራት እና የሁለተኛ ዙር የሌማት ትሩፋት ስራዎች አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት 271ሺ 173 ለሚሆኑ የከተማው ሥራ ፈላጊ ነዋሪዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ትችሏል፡፡
ይህም የዕቅዱን 102% እንደሆነና የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች 216ሺ 659 የሚሆኑት የልል እና የቴክኒካል ክህሎት ስልጠና እንዲወስዱ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በተፈጠረው የስራ ዕድል 9ሺ 228 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ተመስርተው ወደ ሥራ መግባታቸውም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ያሉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጥራቱ በየነ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ መድረኩ ሥራው እየተመራበት ያለበትን አግባብ በመገንዘብ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ይረዳል፡፡
ከወጣቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር በከተማው ለወጣቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ብልፅግና ጽ/ቤት ም/ኃላፊና ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ በበኩላቸው ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በስራ ዕድል ፈጠራና የሌማት ትሩፋት ስራዎች አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን በመግለፅ አሁንም የወጣቶች አመለካከት ቀረፃ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በቀሪ ጊዜያት ከኢንተርፕራይዝ ምስረታ፣ ብድር አቅርቦት ፣በድጋፍ የሚሰጡ ሼዶችን በፍትነት ወደ ስራ ከማስገባት እና ሶስተኛ ዙር ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ በስኬት እንዲጠናቀቅ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ መስጠታቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡










