Mols.gov.et

የሠራተኛውን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ምርታማነቱን ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ ፡፡

May 1, 2024
የሠራተኛውን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ምርታማነቱን ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በአዲስ አበባ የዓለማቀፉ የሠራተኞችን ቀን በሚከበርበት መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በዚህም የዓለም አቀፉን የሠራተኞች ቀን ስናከብር ሠራተኛው መብቱን በተደራጀ መንገድ ለማስከበር ያለፈበትን የትግል ታሪክ ሂደት በመዘከርና ታጋዮቹን በማክበር ብቻ ሳይሆን የአሁኑን የሚመጥን እና የቀጣዩን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ሥራ ለመስራት ቃላችንን በማደስ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ በሀገራችን ከሠራተኛው በየጊዜው የሚነሱ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመመለስ ጥናት ላይ ተመስርቶ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በተለየ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ተቀራርቦ እየሠራም እንደሆነ በመድረኩ ላይ አንስተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢንዱስትሪ ሰላምንና የሙያ ጤንነትና ደህንትን ለማረጋገጥ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነቱን ለማሻሻል እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል አዲስ እሳቤ ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ የሚሆነው እና የሠራተኛው መብትና ጥቅም በዘላቂነት የሚከበረው ምርታማነቱ ሲያድግ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም አሠሪው የሠራተኛው ሁለንተናዊ ብቃቱ እንዲያድግ፣ የሙያ ጤንነቱና ደህነቱ እንዲከበር ማድረግ እንዲሁም ምቹ የሥራ ከባቢ መፍጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የሙያ ደህንነትና ጤንነት እንዲሁም የሥራ ሁኔታዎች ቁጥጥር ጋር ተያይዞ የዘርፉ ማነቆ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት መሆኑን የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር ችግሩን ለመሻገር በዘርፉ በቂ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚያስችል ሥርዓተ ስልጠና ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ሥራውን በቴክኖሎጂ ለማገዝም ሰፊ ጥረቶች እተደረጉ ነው ብለዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርታማነትን ለማሳደግ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣጥ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ፣ ምርታማነትን እንዲያድግ እና የአሠሪና ሠራተኛው ጥቅም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ሁሉም በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ካሣሁን ፎሎ በበኩላቸው፤ የሠራተኞች መሰረታዊ ጥያቄዎች በሂደት ምላሽ እንዲያገኙ ከመንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
en_USEN
Scroll to Top