Mols.gov.et

“የሥራ ዕድል ፈጠራ ከክህሎት ጋር ተሳስሮ ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡” ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

July 10, 2023
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ህብረትና ከኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ ጋር በጋራ ያዘጋጀው የአፍሪካ የመጀመሪያው የሥራ ጉባዔ ተጠናቋል፡፡ በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች እና ባለሙያዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም ለተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የእውቅናና ሽልማት አበርክተዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የአፍሪካ የሥራ ጉባኤ ተጨባጭ ውጤቶችን ሊያስገኝ በሚችል መልኩ ተካሂዷል፡፡ ከሥራ ዕድል አኳያ ያሉ ዕድሎችም ሆኑ ፈተናዎች የአፍሪካውያን የጋራ አጀንዳችን ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ የተጣለው መሰረት አድጎ ኢትዮጵያን ከሌሎች የአፍሪካ እህትና ወንድሞቻችን ጋር በመሆን በርካታ አፍሪካዊ ጉዳዮቻችንን እንደተወጣን እና እየተወጣን እንዳለ ሁሉ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ራስ ምታት የሆነውን ሥራ አጥነትን ለመቀነስ በጋራ ትርጉም ያለው ሥራ እንሰራለን፡፡ ይህም ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ በማሣለጥ ሂደት የበኩላችንን ሚና መጫወት የምንችል ለመሆኑ አብይ ማሳያ ሆኖ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ስለሆነም መንግስት ለሥራ ዕድል ፈጠራው ትልቅ ትኩረት የሰጠው ሲሆን የሥራ ዕድል ፈጠራ ከክህሎት ጋር ተሳስሮ ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ፣ ማነቆዎች እንዲፈቱ እና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመንግስት የቅርብ ድጋፍና ክትትልም እያገኘ ነው ብለዋል፡፡ የዘርፉን ስኬታማነት ለማረጋገጥም ክልሎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት፣ በየደረጃው ያሉ የዘርፉ መዋቅርና ኢንተርፕራይዞች የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ጠቅሰው ክብርት ሚኒስትር በዚህም በሥራቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አንድ ማዕከላትና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም ወደሚቀጥለው እርከን ለተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን እውቅና እንዲሰጣቸው እንደተደረገ ጠቁመዋል፡፡
somSOM
Scroll to Top