Mols.gov.et

ምርምር፣ ፈጠራና አጋርነት የዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረቶች ናቸው ዶ/ር ብሩክ ከድር

June 14, 2026
ምርምር፣ ፈጠራና አጋርነት የዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረቶች ናቸው ዶ/ር ብሩክ ከድር የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ምርምር ኮንፈረንስና የቴክኖሎጂ ውድድር በስኬት ተጠናቋል። መድረኩ ከ16 በላይ ሃገራት ተወዳዳሪዎች፣ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና የዘርፉ ተዋናዮችን በአንድ ያገናኘ ነው። የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ብሩክ ከድር በመዝጊያ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምርምር፣ ፈጠራና አጋርነት የዘላቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረቶች ናቸው ብለዋል፡፡ የመጪውን ዘመን ፍላጎት የሚመለስ የክህሎት ልማት ስርዓት ለመገንባት የምርምር ባህልን ማጠናከር፣ ፈጠራን ማበረታታት እና ከኢንዱስትሪ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር ማስፋት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል። በኮንፈረንሱ 85 የምርምር ጽሑፎች ቀርበው 31 ጥራት ያላቸው ጥናቶች ለመድረክ የተመረጡ ሲሆን፣ 29 የምርምር ሥራዎች በዲጂታል ሽግግር፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ በኢንዱስትሪ 4.0፣ በአረንጓዴ ክህሎቶች፣ በታዳሽ ኃይል እና በአካታች የቴክኒክና ሙያ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በቴክኖሎጂ ውድድሩ ከ10 አገራት የተውጣጡ 35 ፈጠራዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃዎችን በመያዝ እንደ ሃገር ያለንን የፈጠራ አቅም አሳይተዋል። በቴክኖሎጂ ውድድሩ የIoT Smart Irrigation System አንደኛ ደረጃን ሲያገኝ፣ የCerebro Logic ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። የናይጄሪያው Eco-Bin Revenue Intelligence and Traceability System ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን በማግኘት የነሃስ ሜዳሊያ ተሸልሟል። በመድረኩ በአንጎል ውስጥ ግፊትን ያለ ቀዶ ሕክምና ለመለካት የሚችለውን Cerebro Logic የተሰኘ ቴክኖሎጂን የሰሩት ወጣት ሴት የፈጠራ ባለሙያዎች ልዩ አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡ የቀረቡት ጥናቶችና ፈጠራዎች በወረቀት ላይ ብቻ ሳይቀሩ ወደ ተግባርና ወደ ገበያ እንዲሸጋገሩ የፈጠራ ማበልጸጊያ ማዕከላት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥርዓቶች እና የምርምር ትብብሮች የበለጠ መጠናከር እንዳለባቸው ዶ/ር ብሩክ አሳስበዋል።
somSOM
Scroll to Top