የሥራ ዕድል ፈጠራ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት …
November 4, 2026
የሥራ ዕድል ፈጠራ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የልማት አጋሮች ጠንካራ ትብብር ወሳኝ ነው።
ክቡር አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ
የልማት አጋር ድርጅቶች የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የተያዙ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ድጋፋቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው ከአውሮፓ ሕብረት ልዑክ እና ከጀርመን የልማት ትብብር (GIZ) ተወካዮች ጋር በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ወደፊት በትኩረት ተጠናክረው መቀጠል በሚገባቸው የትብብር መስኮች ላይ አተኩረው ተወያይተዋል።
ክቡር አምባሳደር የልማት አጋሮች በዘርፉ እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀው፣ በተለይም የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በሚቀይሩ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት ላይ የጋራ ጥረትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ የሥራ ዕድሎችን ለዜጎች ለመፍጠር የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የልማት አጋሮች የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመው የሚፈጠረው የሥራ ዕድል በቁጥር የሚለካ ብቻ ሳይሆን ዜጎች ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው፣ ኢኮኖሚያዊ ነፃነታቸውን እንዲያጎለብቱና የኑሮ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያስችል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የGIZ ተወካዮች በበኩላቸው በኢኮኖሚ ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎትና ትምህርት ልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በስደተኞች ማኅበራዊ ተሳትፎ ዙሪያ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማጠናከር ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።






