Mols.gov.et

“የኢንዱስትሪ ሰላም ለምርታማነት፣ ምርታማነት ለሀገራዊ ብልጽግና!”

March 12, 2026
“የኢንዱስትሪ ሰላም ለምርታማነት፣ ምርታማነት ለሀገራዊ ብልጽግና!” የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እና ለምርታማነትና ተግዳሮት የነበሩ ትርክቶችን ለመቀየር የሚያስችል አዲስ የሪፎርም እሳቤን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ግንኙነት ዴስክ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘለለው የሚኒስቴር መ/ቤቱ አዲስ የዘርፍ እሳቤ የኢንዱስትሪዎችንና የሠራተኞችን ተወዳዳሪነት የሚያልቅ ብሎም አቀፋዊ ዕድሎችንና ተግዳሮቶችን በአግባቡ የቃኘ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ስለ ምርታማነት የሚነሱ ትርክቶች ብዙ ጊዜ በሁለት ተቃራኒ ጎራዎች እንደሚፈረጁ የሚገልጹት አቶ ውብሸት፤ በአንድ በኩል አሠሪዎች “ሠራተኛው ዝቅተኛ የሥራ ዲሲፕሊንና ክህሎት፣ የሥራ ባህል የሌለው፣ መብቱን ብቻ የሚጠይቅ፣ ግዴታውን የማይወጣና ምርታማነቱ ዝቅተኛ ነው” የሚል ትርክት እንደሚያራምዱ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ሠራተኞች “ሰብአዊ ክብራችን፣ ጤንነታችንና ደህንነታችን የማይጠበቅ እንዲሁም በሕግ የተቀመጠ መብታችንን እንዳንጠቀም ክልከላ ይደረግብናል፤ ለምርትና ምርታማነት የሚያጎለብቱ ሐሳቦች ቢኖሩንም የሚሰማን ባለመኖሩ ምርታማነታችን ቀንሷል” በሚል አሠሪዎችን ሲከስሱ ይደመጣል፡፡ መሰል አመለካከቶች ሥር መስደዳቸውና “የበዝባዥና ተበዝባዥ” ትርክት መጎልበቱ በኢንዱስትሪዎች ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጥሩና በኢንዱስትሪ ሰላም ላይ ጥላ ሲጥሉ ቆይተዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያመላክቱት ምርታማነትን ከሰው ክብርና ጥቅም ነጥሎ ማየት እንደማይቻልም የሚሉት አቶ ውብሸት ሚኒስቴሩ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን በምርትና ምርታማነት ላይ ምክክር በማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን መፍታት የሚችል እና የኢኮኖሚ ሽግግርን የሚያረጋግጥ አዲስ የኢንዱስትሪ ባህል ለመገንባት ላለፉት ዓመታት “የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ ምክክር ለምርታማነት” ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዳሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በማደራደርና በማስማማት ፈጣን መፍትሔ የሚያገኙበት አሠራር በመዘርጋቱ የሥራ ማቆም አድማዎችንና የሥራ መስተጓጎሎችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል። በሌላ በኩል ሠራተኛው ስለ መብቱና ግዴታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች የሥራ ተነሳሽነትንና ዲሲፕሊንን በማጎልበት የኢንዱስትሪዎችን የምርት ጥራትና ብዛት ማሳደግ ተችሏል። ኢንዱስትሪ ማኅበረሰቡ (አሠሪ፣ ሠራተኛና መንግሥት) በጋራ በሚያደርጉት ምክክር፣ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ስልታዊ አቅጣጫዎች እየተቀመጡ ይገኛሉ። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር “የኢንዱስትሪ ሰላም ለምርታማነት” የሚለውን መሪ ሃሳብ ለማሳካት፣ የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ምክክር ቀጣይነት ባለው መልኩ እስከ ታችኛው የዘርፉ መዋቅር እንዲሰርጽ በትኩረት እየሠራ መሆኑ የኢንዱስትሪው ማኅበረሰቡ ለምርታማነትና ለሀገራዊ ብልጽግና በጋራ የሚቆምበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አቶ ውብሸት ዘለለው ገልጸዋል።
somSOM
Scroll to Top