Mols.gov.et

ለሀገር አቀፍ የግብርና ናሙና ቆጠራ በቴክኖሎጂ ታግዞ የተደረገው የሰው ሃይል ምልመላ ሂደት ውጤታማ እንደነበር ተገለፀ፡፡

August 15, 2024
ለሀገር አቀፍ የግብርና ናሙና ቆጠራ በቴክኖሎጂ ታግዞ የተደረገው የሰው ሃይል ምልመላ ሂደት ውጤታማ እንደነበር ተገለፀ፡፡ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት ለሚያካሂደው የግብርና ናሙና ቆጠራ የሰው ሃይል ምልመላ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በለማው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለማከናወን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወሳል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚልና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር በከር ሻሌን (ዶ/ር) ጨምሮ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የምልመላ ሂደቱ ተገምግሟል፡፡ በመድረኩ 43,500 የመስክ መረጃ ሰብሳቢዎችን ለመቅጠር በወጣው ማስታወቂያ መሰረት በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ለሥራው ማመልከታቸው ተመላክቷል፡፡ በዚህም በሁሉም ክልሎች ባሉ ቀበሌዎች ደረጃ ታሳቢ ባደረገ የምዝገባ ስርዓት መስፈርቱን የሚያሟሉ 73 ሺህ የሚሆኑ ዕጩዎች አጭር የጽሁፍ መልዕክት ተልኮላቸው ፈተናውን በኦን ላይን በተሳካ ሁኔታ እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለውጭ ሀገር ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የማይተካ መሆኑንም ማረጋገጥ እንደተቻለም ነው የተገለፀው፡፡ በተሰራው የቅንጅት ሥራ ለለማው ስርዓት እና በቅንጅት ሥራዎች ላይ በርካታ ልምዶች የተገኙበት እንዲሁም በዲጂታል ስርዓት ከአድሎ የፀዳ፣ ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረውን ሀገራዊ ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡ በቀጣይ ፈተናውን ላለፉ እጪዎች አጭር የጽሁፍ መልዕክት በእጅ ስልካቸው እንደሚላክና ያንን መሰረት በማድረግ በየደረጃው ያሉ የሥራና ክህሎት መዋቅር የሥራ ውል ቅጽ የማስሞላት ሥራ ይከናወናል ተብሏል፡፡
somSOM
Scroll to Top