Mols.gov.et

ድህነትን የምናሸንፈው በእውቀት፣ በክህሎት እና በጠንካራ ሥራ ነው! — ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ

January 6, 2026
ድህነትን የምናሸንፈው በእውቀት፣ በክህሎት እና በጠንካራ ሥራ ነው! — ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ድህነትን በዘላቂነት ማሸነፍ የሚቻለው በእውቀት፣ በክህሎት እና በጠንካራ የሥራ ባህል መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ። ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን የገለጹት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዘርፉ አዳዲስ እሳቤዎችና መመሪያዎች ዙሪያ በአማራ ክልል በጎንደር እና በደብረብርሃን ክላስተር ለሚገኙ የዘርፉ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለሙያዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫና የሥልጠና መድረክ ላይ ነው። በመድረኩ በሥራ ዕድል ፈጠራ መስክ የተቀረጹ አዳዲስ እሳቤዎች፣ የአሠራር ሥርዓቶችና መመሪያዎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሥራ አጥነት ችግር ዋነኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና መሆኑን በማንሳት፣ መንግሥት የሥራ አጥነት ምጣኔውን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያውያን ፖለቲካዊ ነፃነታችንን በማስከበር ረገድ ደማቅ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነታችንን ሙሉ በሙሉ ባለመጎናጸፋችን፣ ድህነት በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና እንዳናደርግ አድርጎን ቆይቷል ብለዋል። ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ መንግሥት ትልቅ ርዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀረጻቸው አዳዲስ እሳቤዎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት መስኩ ተስፋ ሰጪና ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል። በክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ የታቀዱ የሪፎርም አጀንዳዎችን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የአማራ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶ/ር ስቡህ ገበያው በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ በዘርፉ አዳዲስ እሳቤዎች ላይ ለአመራሩና ለባለሙያዎች ተቀራራቢ ግንዛቤ ለመፍጠር መድረኩን በባዘጋጀቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
somSOM
Scroll to Top