የቴክኖሎጂ ባለቤቶች በገበያ ላይ ያላቸውን
April 16, 2026
የቴክኖሎጂ ባለቤቶች በገበያ ላይ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ የሆነ ስምምነት
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመ።
የስምምነቱ ዋና ዓላማ በ”ክህሎት ኢትዮጵያ” ፕሮግራም የሚፈልቁ የፈጠራ ስራዎች ህጋዊ የአእምሯዊ ንብረት እውቅና እና ጥበቃ እንዲያገኙ ማስቻል ነው።
ከፊርማው ቀደም ብሎ የባለስልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች በኢንስቲትዩቱ የሚገኙ የፈጠራ ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን እነዚህን ውጤቶች እንዴት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚቻልም መክረዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር የክህሎት ኢትዮጵያ የፈጠራ ፕሮግራም ሀገሪቱን በተለያዩ ዘርፎች ሊለውጡ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች የሚፈልቁበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የፈጠራ ባለቤትነት እውቅና ማግኘት ፈጣሪዎች ለስራዎቻቸው ህጋዊ ጥበቃ እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክቶቻቸውን ለማሳደግ ከሚያግዙ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር እና በገበያ ላይ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አያይዘውም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ችግር ፈቺ ስራዎች እውን እንዲሆኑ ተቋማት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው በማሳሰብ ላለፉት ሁለት ዙሮች የተከናወኑ ተግባራትንና ለሦስተኛው ምዕራፍ የታቀዱ ዝግጅቶችን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እራሷን እንድትችልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ለፈጠራ ስራዎች እውቅና መስጠት ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በዚህ ዘርፍ ላይ በስፋት ባለመሰራቱ ምክንያት የፈጠራ ባለሙያዎች ተስፋ የመቁረጥና የመገታት እንቅፋት ሲገጥማቸው መቆየቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ባለስልጣኑ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀዳለ ተክሉ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው ትብብር ከመጀመሪያው ጀምሮ የጠነከረ መሆኑን ገልጸዋል። የፈጠራ ስራዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው ምክንያት እስካሁን ይገጥሙ የነበሩ በርካታ ችግሮች በዚህ አዲስ ስምምነት አማካኝነት መፍትሄ እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።






