የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተቋማት የችግር ፈቺ መፍትሄዎች ምንጭ
March 27, 2026
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተቋማት የችግር ፈቺ መፍትሄዎች ምንጭ እና የሀብት መፍጠሪያ ማዕከላት እንዲሆኑ ማስቻል
በድሬዳዋ ከተማ ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኝ መምህራን በአዲሱ የኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ እንዲሁም የመሰረታዊ ክህሎት (Basic skill modules) ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ።
ይህ አዲስ ስትራቴጂ ‹‹ከስልጠና በላይ›› በሚል መሪ ቃል የተቀረጸ ሲሆን ዋና ዓላማውም የሰልጣኞችን የአስተሳሰብ አድማስ በማስፋት ተቋማት የችግር ፈቺ መፍትሄዎች ምንጭ እና የሀብት መፍጠሪያ ማዕከላት እንዲሆኑ ማስቻል ነው።
ስትራቴጂው በተለይም በፋብሪኬሽን ኢንጅነሪንግ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
የስልጠናው ይዘት በዋናነት አራት ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮችን የተከተለ ሲሆን እነሱም የዘርፉን አስተዳደር ማጎልበት፣ የስልጠናውን አግባብነትና ጥራት ማረጋገጥ፣ ሰልጣኞችን ለሥራ ዝግጁ የሚያደርጉ ክህሎቶችን ማስታጠቅ እንዲሁም ምርምርና ፈጠራን ማበረታታት ናቸው።
ስልጠናው ገበያ መር መሆኑ የሥራ ገበያው የማይፈልገውን ሙያ በማሰልጠን የሚባክነውን ሀብትና የሚፈጠረውን ሥራ አጥነት ለመቀነስ እንደሚያስገድድ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ውስጥ የተቀረጹ አምስት መሰረታዊ የክህሎት ሞጁሎች ለአሰልጣኞቹ ቀርበዋል።
አነዚህም ልል ክህሎቶች (Soft Skills) ፣ መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎቶች፣ ስነ-ምግባርና ዜጋዊ ኃላፊነት፣ የሥራ ፈጣሪነት አስተሳሰብን ማሳደግ እንዲሁም የንግድ ሥራዎችን መንደፍና ማስጀመር የሚሉ ናቸው።
እነዚህ ሞጁሎች ሰልጣኞች ከመደበኛው የተግባር ስልጠና በተጨማሪ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሥራ ዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ሁለንተናዊ ብቃት እንዲላበሱ ለማድረግ ታስበው የተዘጋጁ መሆኑ ተጠቅሷል።






