የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የመንግስት አስተዳደር አገልግሎት ሪፎርም ትግበራ ለሌሎች ተቋማት አርአያ መሆኑ ተገለጸ
February 3, 2026
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የመንግስት አስተዳደር አገልግሎት ሪፎርም ትግበራ ለሌሎች ተቋማት አርአያ መሆኑ ተገለጸ
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሱፐርቪዥን ቡድን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በመገኘት፣ ተቋሙ የጀመረውን የተቀናጀ የሪፎርም እሳቤ እና ወደ ተግባር ምዕራፍ የተሸጋገሩ ሥራዎችን የመስክ ምልከታና የድጋፍ ሥራ አከናውኗል።
የሱፐርቪዥን ቡድኑ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባደረገው ቆይታ፣ ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥና የአስተዳደር ማሻሻያ ተግባራትን ወደ ወሳኙ “የተግባር ምዕራፍ” ማሸጋገሩን አረጋግጧል።
ይህም ሚኒስቴሩ እንደ ሀገር የተቀመጠውን የሪፎርም ግብ ለማሳካት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበትና ለሌሎች የመንግስት ተቋማትም አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑ ተመልክቷል።
ዲጂታላይዜሽን እና የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO) በምልከታው ወቅት ሚኒስቴሩ ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተገበራቸው የሚገኙ ቁልፍ ሥራዎች በበጎ ተነስተዋል፡፡
ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ዜጎች ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና እንግልት የሌለበት አገልግሎት የሚያገኙባቸው አሰራሮች መዘርጋቱም ተገልጿል፡፡
የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም ተቋማዊ ሥራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ የማድረግ ሂደት ትልቅ እመርታ አሳይቷል።
ሚኒስቴሩ የሪፎርም እሳቤዎችን እና አዳዲስ ፖሊሲዎችን በዋናው መስሪያ ቤት ብቻ ሳይወሰን፣ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በማውረድ ክልሎችን ለማብቃት እያደረገ ያለው ድጋፍ የሪፎርሙን ውጤታማነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ተጠቁሟል። በክልሎች ደረጃ የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች መጀመራቸውም እንደ አንድ ትልቅ ጥንካሬ ተነስቷል።
በትግበራ ምዕራፍ የታቀዱ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ቀጣዩ “የማፅናት ምዕራፍ” ለመሸጋገር ተቀናጅቶና ተናቦ መሥራት እንደሚገባ በኮሚሽኑ ድጋፍና ክትትል ቡድን ተጠቁሟል፡፡






