Mols.gov.et

ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ከክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ጋር የሥራ ርክክብ አደረጉ

October 13, 2026
ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ከክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ጋር የሥራ ርክክብ አደረጉ አዲስ የተሾሙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ በሚኒስቴሩ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ ከነበሩት ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ጋር የሥራ ርክክብ አድርገዋል። በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፣ በዘርፉ የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን፣ የተመዘገቡ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና የቀጣይ ሥራ አቅጣጫዎችን የሚያብራራ ሰነድ አስረክበዋል። ክቡር አቶ ዳንኤል፣ በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር ለማስቀጠል ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ ትጋትና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በተቋሙ በነበራቸው የሥራ ጊዜ ለተደረገላቸው ትብብር አመስግነው፣ አዲስ ለተሾሙት ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የተሳካ የሥራ ዘመን ተመኝተዋል። ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፣ በዘርፉ የተጀመሩ ሥራዎችንና የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክረው በማስቀጠል፣ ያሉ ማነቆዎችን በመለየትና በመፍታት ለዘርፉ ውጤታማነት የሚያግዙ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በቀጣይም በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን በጥልቀት ለመለየት፣ ተገቢ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመቀየስና የዘርፉን የሥራ አፈጻጸም ለማሻሻል ቀጣይነት ያለው ውይይትና ምክክር እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
somSOM
Scroll to Top