Mols.gov.et

ፍትሃዊ የፋይናንስ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረው የማለዳ ውይይት

January 1, 2026
ፍትሃዊ የፋይናንስ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረው የማለዳ ውይይት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን፣ ፈጠራን ማዕከል ያደረገና ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል የፐብሊክ ሴክተር ኢኖቬሽን ላብ አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ይሀንን መነሻ በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት፣ አዳዲስ ሃሳቦችን ለማመንጨት እና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመላከት በየወሩ የሚኒስቴሩ እና የተጠሪ ተቋማትየሥራ ኃላፊዎች እና የማኔጅንት አባላት የሚሳተፉበት የማለዳ ውይይት ይካሄዳል፡፡ የዛሬው ውይይት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅርቡ የተፈራረማቸውን የትብብር ስምምነቶች ወደ መሬት ማውረድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አተኩሮ ተካሂዷል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል፤ ምንም እንኳን ኢንተርፕራይዞችና ስታርታፖች የሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ቢሆኑም ሥራቸውን በሚጠበቀው ልክ እንዳያሳኩ የፋይናንስ አቅርቦት ዋነኛው ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ክብርት ሚኒስትር ባቀረቡት ማብራሪያ በሀገራችን 70 በመቶ የሚሆኑ የሥራ ዕድሎች በኢንተርፕራይዞች እንደሚፈጠሩ ጥናቶችን ጠቅሰው ልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ኢንተርፕራይዞች 80 በመቶ የሚሆኑት ማደግ እና መስፋፋት ቢፈልጉም በብድር አቅርቦት ምክንያት እድገታቸው እንደሚገታና የፋይናንስ ተደራሽነት ችግር የብዙ ሥራ ፈጠራሪዎች ችግር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ የኢንተርፕራይዞችና የስታርታፕ ቢዝነሶችን የፋይናንስ ችግር በመፍታት በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ሲያካሄድ በቆየው ውይይት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ስምምነቶቹን ወደ ዕቅድ ቀይሮ የሚጠበቀውን ውጤት ለማሳካት በየደረጃው ከተለወጠው ሁኔታ ጋር የተለወጠ አካሄድ መኖር እንዳለበት ጠቁመው ለተግባረዊነቱ ሁሉም አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስምምነቶቹ ለሥራ፣ ለፈጠራ እና ለኢንተርፕሪነርሺፕ ስነ-ምህዳር ግንባታ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው የትብብር ማዕቀፎቱ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያሳኩ ያስችላሉ ያሏቸውን ሀሳቦች በዝርዝር አንስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡
somSOM
Scroll to Top