ከስደት ተመላሽ ዜጎችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ ወደ ሥራ
February 5, 2026
ከስደት ተመላሽ ዜጎችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ ወደ ሥራ የማስገባት ተግባር በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለፀ
‹‹አካታችነት›› በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ የዋለው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡
በዚሁ መሰረት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሰጡ ስልጠናዎች ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ወጣቶችን ስደተኞችንና ሌሎችም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በእኩል ተደራሽ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይጠበቃል፡፡
የትኩረት አቅጣጫውን ወደ ተግባር ለመለወጥ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም በአስተዳደሩ ሥራና ክህሎት ቢሮ እንዲሁም የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት በሥደተኞች ላይ በሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተጎብኝተዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ ወጣቶችንና ተመላሾችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ ይገኛል።
ስልጠናው ወጣቶች በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ እንዲሰማሩና የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ እንዲመሰርቱ የሚያስችል ሲሆን ይህም ከጥገኝነት መንፈስ ተላቀው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እድል የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ስደትን በዘላቂነት ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተገልጿል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው በድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እየተከናወነ ያለው ተግባር መልካም መሆኑን ገልጸው በተለይም ወጣቶች የሚያገኙትን እውቀት ወደ ገቢ ምንጭ በመቀየር የተሻለ ህይወት እንዲመሩ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ለሌሎች አካባቢዎችም አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። መረጃው የድሬዳዋ ሥራና ክህሎት ቢሮ ነው፡፡


